ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ 1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 16 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የስምዖን ልጅ ዮሐንስ ከንዳብዮስን አሸንፎ አባረረ 1 ዮሐንስ ወደ ጌዘር መጣና የከንደብዮስን ሥራ ለአባቱ ለስምዖን ነገረው። 2 ስምዖን ሁለቱን ታላላቆቹን ልጆቹን ይሁዳንና ዮሐንስን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “እኔና ወነድሞቼ እንዲሁም የአባቴ ቤት ከልጅነታችን ጀምረን እስከ ዛሬ ድረስ ከእስራኤል ጠላቶች ጋር ተዋግተናል፤ ብዙ ጊዜም እስራኤልን ለማዳን ዕድል አግኝተናል። 3 አሁን እኔ አርጅቻለሁ፤ እናንተም አሁን በእግዚአብሔር ምሕረት በዕድሜ ከፍ ብላችኋል፤ ስለዚህ የእኔንና የወንድሜን ቦታ ይዛችሁ ሂዱ፤ ስለ ሕዝባችን ተዋጉ፤ የእግዚአብሔር እርዳታ ከእናንተ ጋር ይሁን።” 4 ከሀገሩ ሃያ ሺህ የጦር ሰዎች፤ እግረኞችና ፈረሰኞችን መረጠ፤ ከንደብዮስን ለመውጋት ገሠገሠ፤ በዋዲን አዳር ሆነ። 5 ከዚህ በኋላ በማለዳ ተነስተው ወደ ሜዳው ሂዱ፤ እነሆ ብዙ እግረኛና ፈረሰኛ ጦር ውጊያ ለመግጠም ወደ እነርሱ ይመጡ ነበር፤ በመካከላቸው ወንዝ ነበር፤ 6 ዮሐንስና የእርሱ ሰዎች በእነርሱ ፊት ተሰልፈው ቦታ ቦታቸውን ያዙ፤ እነርሱ ወንዙን ለመሻገር የማይደፍሩ መሆናቸውን አውቆ ዮሐንስ ቀድሞአቸው ወንዙን ተሻገረ፤ የእርሱ ሰዎች ይህን አይተው እሱን ተከትለው ተሻገሩ። 7 ፈረሰኛ ጦሩን በእግረኛ ጦር መካከል በማድረግ ወታደሮቹን ከፋፈለ፤ ምክንያቱም የጠላት ፈረሰኛ ጦር በጣም ብዙ ነበርና ነው። 8 መለከት ተነፋ፤ ከንደብዮስ ከነሠራዊቱ ተሸነፈ፤ ብዙዎቹ ቆስለው ወደቁ፤ የቀሩት ወደ መሽጉ ሸሽተው ሄዱ። 9 በዚያን ጊዜ የዮሐንስ ቴድሮን ድረስ ተከታተላቸው። 10 የሸሹት ሰዎች በአዛጦስ ገጠር እስካሉት ግንቦች ድረስ ሄዱ፤ ዮሐንስ በእሳት አጋያቸው፤ ከጠላት ወገንም አስር ሺህ ሰዎች ሞቱ፤ ዮሐንስ በሰላም ወደ ይሁዳ አገር ተመለሰ። የስምዖን አሳዛኝ አሟሟት በዶክ፤ ዮሐንስ የአባቱን ቦታ መተካቱ 11 የአቡቦስ ልጅ ጰጠሎሜዎስ የኢያሪኮ በረሃ ሜዳ አዛዥ ሆኖ ተሹሞ ነበር። ብዙ ብርና ወርቅ ነበረው፤ 12 ምክንያቱም እርሱ የሊቀ ካህናቱ አማች ነበረ፤ 13 ፍላጐቱም በመቀስቀሱ እራሱን የሀገሮች ሁሉ ገዢ ለማድረግ ፈለገ፤ ስለዚህም ስምዖንንና ልጆቹን ለማጥፋት የተንኮል ሐሳብ አደረበት። 14 ስምዖን ሰለሀገሪቱ ከተሞች አስተዳዳር ወዲያ ወዲህ እያለ ይደክም ነበረ፤ ከልጆቹ ከማታትያስና ከይሁዳ ጋር ወደ ኢያሪኮ ወረደ፤ የወረደውም በመቶ ሰባ ሰባት (የካቲት 134) ዓመተ ዓለም የሰባጥ ወር በሆነው በአሠራ አንደኛው ቀን ነው። 15 የአቡቦስ ልጅ በተንኮል በአንዲት ትንሽ ምሽግ ውስጥ ተቀበላቸው። ይህቺ ምሽግ እርሱ የሠራት ዶክ የምትባል ምሽግ ናት። ትልቅ ግብዣ አዘጋጀላቸው፤ ግን በምሽጉ ውስጥ ሰዎችን ሸሸገ። 16 ስምዖንና ልጆቹ ጠጥተው ሞቅ ባላቸው ጊዜ ጰጠሎሜዎስና የእርሱ ሰዎች ተነሥተው የጦር መሣሪያቸውን እነሡና በግብዣው አዳራሽ ውስጥ ስምዖንን ከበቡት፤ እንዲሁም ሁለቱን ልጆቹንና ከአገልጋዮቹ አንዳንዶቹን ገደሉ። 17 በእንዲህ ዓይነት ትልቅ የከዳተኛነት ሥራን ሠራ፤ ደግ ለሠራለት በክፉ መለሰ። 18 ጶጠሎሜዎስ ያደረገውን ነገር ለንጉሡ ጻፈለት፤ ከተሞችንና ገጠሮችን የሚያስረክቡትና የሚረዱት ወታደሮች እንዲልክለትም ጠየቀው። 19 ዮሐንስን ለማጥፋት ሌሎች ሰዎችን ወደ ጌዘር ላከ፤ ብርና ወርቅ፤ ሌላም ስጦታ እንድሰጣችሁ ወደ እኔ ኑ በማለት ለጦር አዛዣች ደብዳቤ ላከ፤ 20 ኢየሩሳሌምንና የቤተ መቅደሱን ተራራ እንዲይዙ ሌሎች ሰዎችን ላከ፤ 21 ግን አንድ ሰው ቀድሞ ሄደና በጌዘር ለዮሐንስ የአባቱንና የወንድሞቹን መሞት ነገረው፤ በተጨማሪም፤ “አንተንም ለመግደል ሰው ልኳል” ሲለ ነገረው። 22 ይህን በሰማ ጊዜ ዮሐንስ በጣም ደነገጠ፤ ሊገድሉት የመጡት ሰዎች ይዞ ገደላቸው፤ ምክንያቱም እርሱን ለመግደል መምጣታቸውን አውቆ ነበርና። 23 የቀሩት የዮሐንስ ስራዎች፥ ውጊያዎቹ፥ የፈጸማቸው መልካም ሥራዎች፥ የሠራቸው ግንቦችና ታላላቅ ሥራዎቹም፤ 24 በአባቱ ምትክ ሊቀ ካህናት ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ የሠራው ሁሉ እነሆ በጊዜው መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ ይገኛል። |