ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ 1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 14 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)የስምዖን ምስጋና 1 በመቶ ሳባ ሁለት (144) ዓ.ዓ ንጉሥ ዲመትሪዮስ ሠራዊቱን ሰብስቦ ትሪፎንን ለመውጋት እርዳታ ፍለጋ ወደ ሜዶን ሄደ። 2 ዲመትሪዮስ ወደ እርሱ አገር መግባቱን ሰምቶ የፋርስና የሜዶን ንጉሥ አርሴቅስ ዲመትሪዮስን በሕይወቱ ይዞ እንዲያመጣው ከጦር መሪዎቹ አንዱን ላከ፤ 3 ይህ የጦር መሪ ሄደና የዲመትሪዮስን ሠራዊት ወግቶ አሸነፈ፤ ዲመትሪዮስን ማርኮ ወደ አርስቄስ አመጣው፤ አርስቄስም እስር ቤት አስገባው፤ 4 ስምዖን በነበረበት ጊዜ ሁሉ የይሁዳ ምድር እረፍት አገኘች፤ እርሱ የሕዝቡን ደኀንነት ይፈልግ ነበር፤ እርሱ በነረበረት ጊዜ ሁሉ ሰዎች በሥልጣኑና በክብሩ ተደሰቱ፤ 5 ኢዮጴን በመያዝ በክብር ላይ ክብርን ጨመረ፤ ኢዮጴን ወደቡና ወደ ማዴትራኒያን ባሕር መሄጃ በር አደረጋት፤ 6 የሀገሪቷን ድንበሮች አስፋፋ፥ በሚገባም መራት፤ 7 ብዙ ምርኮኞችን አሰፈረ፤ ጌዘርን፥ ቤተሱርን፥ ምሽጉንም ያዘ፤ እርኩስ ነገርን ሁሉ ነቅሎ አጠፋ፤ ማንም ሊቋቋመው አልቻለም። 8 ሰዎች ምድራቸውን በሰላም ያርሱ ነበር፤ ምድር ፍሬዋን ትሰጥ ነበር፤ በሜዳው ላይ የበቀሉ ዛፎችም ፍሬአቸውን ይለግሱ ነበር። 9 ሽማግሌዎች በአደባባዮች ተቀምጠው ስለብልጽግና ብቻ ይናገሩ ነበር፤ ጐልማሶች የክብርና የጦር ልብስ ይለብሱ ነበር። 10 ለከተሞች ምግብ አቀረበላቸው፤ የተጠናከሩ ምሽጐች አበጀላቸው፤ በዚህ ዓይነት ዝናው እስከ ምድር ዳርቻዎች ድረስ ተሰማ። 11 በሀገሪቱ ውስጥ ሰላምን አደረገ፤ እስራኤልም ታላቅ ደስታን አገኘች። 12 እያንዳንዱ ሰው በወይኑና በበለሱ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፤ የሚያስፈራቸው ማንም አልነበረም። 13 ከምድራቸው ሊወጋቸው የሚችል ጠላት አልነበረም፤ ነገሠታቱ ሁሉ ተደምስሰዋል። 14 የተጐሳቆሉትንም ሰዎች አበረታታ፤ ተንኮለኞችንና ከሐዲዎችንም ረገጣቸው። 15 ሕጉን ለማስከበር በብርቱ ጣረ፤ ቤተ መቅደስን አዲስ ክብር አለበሳት፤ በበርካታ የተቀደሱ ቁሰቁሶችም አበለጸጋት። ከእስፖርታና ከሮም የነበረው ግንኙነት መታደስ 16 በሮምና በእስፖርታ የዮናታን ሞት ተሰማና ትልቅ ኀዘን ሆነ። 17 ነገር ግን ወንድሙ ስምዖን በእርሱ ምትክ ሊቀ ካህናት መሆኑና የሀገሪቱና የከተሞች ገዥ መሆኑንም ባወቁ ጊዜ 18 ከወንድሞቹ ከይሁዳና ከዮናታን ጋር የተዋዋሉትን ውል በነሃስ ሰሌዳ ላይ ጽፈው ላኩለት። 19 ሕዝቡ በተሰበሰበበት በኢየሩሳሌም ተነበበ። 20 እስፖርታውያን የላኩት የደብዳቤው ግልባጭ እንዲህ ይላል፥ “ሹማምንትና የእስፖርታ ከተማ ለወንድሞቻቸው ለሊቀ ካህናት ሰምዖንና ለሽማግሌዎች፥ ለካህናት ለአይሁድ ሕዝብ ሁሉ ሰላምታ ያቀርባሉ። 21 ወደ ሕዝባችን የተላኩት መልክተኞች ብልጽግናችሁንና ክብራችሁን ነግረውናል፤ በመምጣታቸውም ተደስተናል። 22 እነርሱ የገለጹልንን በሕዝቡ ውሳኔዎች መካከል እንዲህ ስንል ጽፈነዋል፤ የአንጥዮኩስ ልጅ ኑመንዮስና የኢያሶን ልጅ አንጢጰጥሮስ የአይሁድ መልእክተኞች ሆነው ከእኛ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ለማደስ ወደ እኛ መጥተዋል፤ 23 ሕዝቡ ደስ ብሎት እነዚህን ሰዎች በክብር ተቀብለቸዋል፤ የንግግራቸውንም ግልባጭ በሕዝቡ መዝገብ ውስጥ አኑሮታል፤ ይህም የተደረገው የእስፖርታ ሕዝብ እያስታወሰሰው እንዲኖር ነው። እንዲሁም ግልባጩ ለሊቀ ካህናት ስምዖን ተጽፎል”። 24 ከዚህ በኋላ ስምዖን ከሮማውያን ጋር ያለውን ቃል ኪዳን ለማጽናት አንድ ሺህ ምናን ከሚመዝን ከትልቅ የወርቅ ጋሻ ጋር አመንዮስን ወደ ሮም ላከው። ስለ ስምዖን ንብረት የወጣ አዋጅ 25 ሕዝቡ ይህን ነገር በሰማ ጊዜ እንዲህ አለ፤ “ለስምዖንና ለልጆቹ ምን ውለታ ነው የምንመልሰው? 26 ምክንያቱም እርሱና ወንድሞቹ፤ የአባቱም ቤት ሁሉ ጠንካሮች ሆነው ተገኝተዋል፤ በጦር መሣሪያ የእስራኤልን ጠላቶች አጥፍተዋል፤ ለሕዝቡ ነጻነትን አስገኝተዋል”። ስለዚህም ይህንን ክቡር ተግባር በብረት (በነሐስ) ሰሌዳ ላይ ጽፈው፤ በሐውልት ላይ አድርገው በጽዮን ተራራ ላይ አቆሙት፤ 27 የጽሑፍ ግልባጭ የሚለው እንዲህ ነው፤ “ኤሉስ በገባ በዓሥራ ስምንት መቶ ሰባ ሁለት (መስከረም 13 ቀን 140 ዓመተ ዓለም) የሊቀ ካህናቱ ስምዖን ሦስተኛ ዓመት ነበር። 28 ያንጊዜ በአሳራማኤል፥ በካህናቱና በሕዝቡ፥ በሀገሪቱ ሹማምንትና ሽማግሌዎች በተደረገው ታላቅ ጉባኤ እንዲህ ሲሉ ለእኛ ለእስራኤላውያን አስታውቀውናል። 29 በሀገሪቱ ላይ በደረሱት የማያባሩ በርካታ ጦርነቶች የኢዮአሪብ ልጆች ዘር የሆነው የማታትያስ ልጅ ስምዖን እና ወንድሞቹ ለአደጋ ተጋልጠዋል፤ ቤተ መቅደሳቸውንና ሕግም ተከብረው እንዲኖሩ በማለት የሕዝባቸውን ጠላቶች ተቋቁመዋል፤ ሕዝባቸውንም ታላቅ ክብር አጐናጽፈዋል።” 30 ዮናታን የእርሱን ሕዝብ ሰብስቦ የእነርሱ ሊቀ ካህናት ሆነ፤ ከዚህ በኋላም በዕረፍቱ ከቀደሙትና ካለፉት አባቶቹ ጋር ተቀላቀለ። 31 ይህን የሰሙ የአይሁድ ጠላቶች አገራቸውን ለመውረርና ለማጥፋት፤ እጃቸውንም በቤተ መቅደሳቸው ላይ ለማንሣት ፈለጉ፤ 32 በዚያን ጊዜ ስምዖን ተነሥቶ ስለ ሕዝቡ ተዋጋ፤ ከገንዘቡም ብዙ ወጪ አድርጐ የብሔራዊ ጦር ሰዎችን አስታወቀ፤ ደሞዛቸውንም ከፈለ። 33 የይሁዳን ከተሞችና በቀድሞ ጊዜ በድንበር ላይ የጠላት ኃይል የነበረውን ቤተሱራን አጠናከረ፤ ከአይሁዳውያን ተዋጊዎች እዚያ አደረገ። 34 በባሕር ኢዮጴን በፊት ጠላቶች ይኖሩባት የነበረችው ጌዘሮን በአዞጥ ድንበር አጠናከረ፤ አይሁዳውያንን አደረገበት፤ የሚያስፈልጋቸውንም ሁሉ እዚያ አስቀመጠላቸው። 35 ሕዝቡ የስምዖን ታማኝነትና ለራሱ ሕዝብ ሊሰጥ ያሰበውን ክብር ተመለከተለት፤ ባደረገው ሁሉ፥ ለሕዝቡ ባሳየው እውነተኛነትና እምነት ምክንያት የእነርሱ መሪና ሊቀ ካህናት እንዲሆን አደረገጉት፤ ምክንያቱም የእርሱ የዘወትር ጥረቱ ሕዝቡን ከፍ ለማድረግ ነበረ። 36 ስምዖን በዘመኑ አረማውያንና በዳዊት ከተማ በኢየሩሳሊም የነበሩትን ሰዎች ከሀገሪቱ ነቅሎ ለመጣል ችሏል፤ እነርሱም እዚያ ምሽጋቸውን አድርገው ነበር፤ ከዚያ እየወጡ የቤተ መቅደሱን ዙሪያ ያረክሱ ነበር፤ ለቅድስናው የማይስማማ ነገር ለማድረግ በብርቱ ይጥሩ ነበር። 37 እርሱ በዚህ ቦታ ላይ የአይሁድ ወታደሮች አደረገና ለሀገሪቱና ለከተማይቱ ጥበቃ አጠናከረው፤ የኢየሩሳሌምን መካበቢያዎች ከፍ አድርጐ ሠራ። 38 ከዚህ በኋላ ንጉሥ ዲሜጥሮስ ሊቀ ካህንነቱን አጸናለት፤ 39 ከወዳጆቹ ቍጥር ውስጥ አገባው፤ ክብርም አቀዳጀው። 40 ሮማውያን አይሁዳውያንን እንደ ወዳጆቻቸው፥ እንደ የጦር ጓደኞቻቸውና እንደ ወንድሞቻቸው የሚያዩዋቸው መሆኑን ተገንዝቦ ነበር፤ 41 አይሁዳውያንና ካህናት አንድ ታማኝ ነቢይ እስኪነሣላቸው ድረስ ስምዖንን ለዘወትር መሪና ሊቀ ካህናት አድርገው መሾማቸውን ሰምቶ ነበር። 42 የጦር መሪና የቤተ መቅደስ ኃላፊ ሆኖ መመረጡን፥ የሥራ መሪዎችንና የሀገር አስተዳዳሪዎችን፥ የጦር መሣሪያና የምሽጐች ኃለፊዎችን ለመሾም መመረጡንም አውቋል፤ 43 የተቀደሱ ነገሮች ኃላፊ ነው፤ ሁሉም ሊታዘዙለት ይገባል፤ የሀገሪቱ ጽሑፎች ሁሉ በስሙ እንዲጻፉ ያደርጋል፤ የከፋይና የወርቅ ልብስ እንዲለብስ ይፈቀድለታል። 44 ከሕዝቡም ሆነ ከካህናት መካከል ማንም እርሱ የደነገገውን ማፈረስ አይገባውም፤ የእርሱን ትእዛዝ መቃወም ወይም ያለ እርሱ ፈቃድ በሀገሪቱ ውስጥ ስበስባ ማድረግ ከፋይ መልበስ ወይም የወርቅ መቆለፊያ ማድረግ ማንም አይገባውም። 45 የእርሱን ሕግጋት የሚያፈርስ ሁሉ ቅጣት ይገባዋል። 46 ሕዝቡ በሙሉ እነዚህን መብቶች ለስምዖን ለመስጠት ተስማማ። 47 ስምዖንም እሺ ብሎ የሊቀ ካህነቱን ሥራና የጦር መሪነቱን፤ የአይሁዳውያንና የካህናት ሹም መሆንን፥ የሁሉ በላይ ራስ መሆንን ተቀበለ። 48 ይህ ቃል በብረት (በነሐስ) ሰሌዳ ላይ እንዲጻፍና በቤተ መቅደሱ ግቢ ውስጥ በሚታይ ቦታ እንዲቀመጥ ወሰኑ። 49 ለስምዖንና ለልጆቹ የሚያገለግሉ የእነዚሁ ግልባጭም በግምጃ ቤት እንዲቀመጡ ተስማሙ። |