Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ

1ኛ መጽሐፈ መቃብያን 12 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ዮናታን ከሮም እና ከእስፖርታ የነበረው ግንኙነት

1 ዮናታን የጊዜው ሁናቴ ለእርሱ ምቹ ሆኖ ስላገኘው ከሮማውያን ጋር የነበረውን ወዳጅነት ለማጽናትና ለማሳደስ ፈልጐ ወደ ሮም የሚልካቸውን ሰዎች መረጠ።

2 እንዲሁም በዚሁ ዓይነት ወደ እስፖርታ ወደ ሌሎችም ቦታዎች ደብዳቤዎችን ላከ።

3 ወደ ሮም የሄዱት መልእክተኞች በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው እንዲህ አሉ፤ “ሊቀ ካህናት ዮናታንና የአይሁድ ሕዝብ ቀድሞ የነበረውን ወዳጅነትና የስምምነት ውል ለማደስ ልከውናል”።

4 ምክር ቤቱም ለእያንዳንዱ አገር ባለ ሥልጣኖች በሰላም ወደ ይሁዳ አገር እንዲያሳልፉቸው ደብዳቤዎች ሰጧቸው።

5 ዮናታን ለእስፖርታ ሰዎች የጻፈው ደብዳቤ ግልባጭ እንዲህ የሚል ነበር፤

6 “ሊቀ ካህናቱ ዮናታንና የሕዝቡ ምክር ቤት፥ ካህናቱ፥ የቀረውም የአይሁድ ሕዝብ ለወንድሞቻቸው ለእስፖርታውያን ሰዎች ሰላምታ ያቀርባሉ፤

7 ከዚህ በታች የሚገኘው ግልባጭ እንደሚመሰክረው ከዚህ ቀደምም በእናንተ ነግሦ ከነበረው ከአሪዮስ የወንድምነት ምልክት የሆነ ደብዳቤ ለሊቀ ካህናት ኦንያስ ተልኳል፤

8 ኦንያስ መልእክተኛውን በክብር አስተናግዷል፤ የስምምነትና የወዳጅነት ጉዳይ ያለበትን ደብዳቤም ተቀብሏል።

9 በእኛ በኩል ይህ ጉዳይ አስፈላጊያችን ባይሆንም የቅዱሳት መጽሐፍትን ጽናት ይዘን የቀደመውንና ከእናንተ ጋር የነበረንን

10 ወንድማማችነት በማደስ ባዕድነትን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው፥ የመጨረሻውን ደብዳቤ ከላካችሁልን እጅግ ብዙ ዘመናት ተቆጥረዋል፤

11 በበዓላትና በሌሎችም ቀናት በምናደርጋቸው መሥዋዕቶችና ጸሎቶች ሁልጊዜ ለወንድሞች መደረግ እንደሚገባና እንደሚያስፈልግ እናንተን ሳናስታውስ ቀርተን አናውቅም።

12 በክብራችሁ እንደሰታለን።

13 እኛ ግን መከራዎችንና ጦርነቶች ደርሰውብናል፤ በዙሪያችን ያሉ ነገሥታም ወግተውናል።

14 በእነዚህ በጦርነቶች ምክንያት እንተና ሌሎችን የጦር ጓደኞቻችንን፤ ወዳጆቻችንን ማስቸገር አልፈልግም።

15 እኛን ለማገዝ ከሰማይ የሚመጣልን እርዳታ አለን፤ እኛ ከጠላቶቻችን እጅ ድነናል፤ እነርሱ ግን ተዋርደው ቀርተዋል፤

16 የአንጥዮኩስን ልጅ ኑምንዩስንና የኢያሶንን ልጅ አንቲጳጠሮስን መርጠን ከሮማውያን ጋር የነበረንን የቀድሞ ወዳጅነታችንንና ስምምነታችንን ለማደስ ወደ ሮማውያን ልከናቸዋል።

17 እንዲሁም ወደ እናንተ መጥተው ሰላምታ እንዲያቀርቡና ስለ ስምምነታችንና ስለ ወንድማዊ ግንኙነታችን ተሐድሶ ጉዳይ ደብደቤ እንዲሰጧቸሁ ልከናቸዋል።

18 ስለዚህ ጉዳይ መልሳችሁን እንጠባበቃለን”።

19 ለኦንያ የተላከው ደብዳቤ ግልባጩ እንዲህ ይላል፤

20 “የእስፖርታውያን ንጉሥ አርዮስ ለሊቀ ካህናት ኦንያ ሰላምታ ያቀርባል፤

21 እስፖርታውያንና አይሁዳውያን ወንድማማች መሆናቸውንና ከአብርሃም ዘር መወለዳቸውን የሚገልጽ ጽሑፍ አግኘተናል።

22 አሁን ይህን ነገር ካወቅን ዘንዳ ስለ መልካም አኗኗራችሁ ብትጽፉል መልካም ነው።

23 እኛም ለእናንተ ያለን መልእክት ይህ ነው። ከብቶቻችሁንና ንብረቶቻችሁ የእኛ ናቸው፤ የእኛዎቹም የእናንተ ናቸው፤ መልእክተኞቻችን ይህን እንዲገለጹላችሁ ልከናቸዋል”።


ናታን የሶርያ በቀል፤ ስምዖን በፍልስጥኤም

24 የዲሜጥሮስ የጦር ሹማምንት ለመዋጋት ፈልገው ከቀድሞ ይበልጥ የበዙ ወታደሮች ይዘው እንደገና መምጣታቸውን ዮናታን ሰማ።

25 ከኢየሩሳሌም ወጣና ሊገጥማቸው ወደ ሃማት አገር ሄደ፤ ምክንያቱም ወደ እርሱ አገር እንዲገቡ ጊዜ ሊሰጣቸው አልፈቀደም።

26 ወደ ሠፈራቸው ሰላዮች ላከ፤ ሰላዮቹ ተመልሰው ጠላቶች በሌሊት ሊወሩን ይዘጋጃሉ ብለው ነገሩት።

27 ፀሐይ ስትጠልቅ ዮናታን ሰዎቹን ነቅተውና የጦር መሣሪያቸውን በእጃቸው ይዘው ሌሊቱን ሙሉ ለውጊያ ዝግጁዎች ሆነው እንዲገኙ አዘዛቸው። እንዲሁም በሠፈሩ ዙሪያ ጠባቂዎች አቆመ።

28 ዮናታንና የእርሱ ሰዎች ለውጊያ ዝግጁዎች መሆናቸውን በሰሙ ጊዜ ጠላቶቹ ፈሩ፤ ልባቸው በፍርሃት ተሞልቶ በሠፈራቸው እሳት አነደዱ።

29 ነገር ግን ዮናታንና ሰዎቹ እሳቱን ያዩ ስለ ነበር መሄዳቸውን ያወቁት ጠዋት ሲነጋ ብቻ ነው።

30 ዮታን ተከታተላቸው፤ ግን አልደረሰባቸውም፤ ምክንያቱም የኤለውጥሮስን ወንዝ ተሻግረው ነበር።

31 ዮናታን ዘብዴያውያን ወደሚባሉ ዓረቦች ተመለስና ወጋቸው፤ ማረካቸው።

32 ከዚያም ሠፈሩን ነቅሎ ወደ ደማስቆስ ሄደ፤ እዚያ አገሩን ሁሉ እየተዘዋወረ ተመለከተ።

33 ስምዖንም ገሠገሠና እስከ አስቃሎንና በአጠገቡ እስካሉት ምሽጐች ድረስ ሄደ። ከዚህ በኋላ ወደ ኢዮጴ ተመለሰና ያዛት።

34 ምክንያቱም የእዚያ አገር ሰዎች ምሽጉን ለዲመትሪዮስ ሰዎች ለመስጠት ፈልገው ስለ ነበር ነው። የሚጠብቋት ወታደሮችም በዚያ አቆመ።


የግንባታ ሥራ በኢየሩሳሌም

35 ዮናታን ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ፤ ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ሰበሰበና ከእነርሱ ጋር ሆኖ በይሁዳ አገር ምሽጐች ለመሥራት ተማከረ፤

36 የኢየሩሳሌም ግንቦችን ለማጠናከርና በምሽጉና በከተማዋ መካከል መለያ የሚሆን ረዥም ግንብ ለመሥራት ፈለገ፤ ይህንንም ማድረግ ያሰበው የዲመትሪዮስ ሰዎች እየመጡ መግዛት ወይም መሸጥ እንዳይችሉ ነው።

37 ከተማውን እንደገና የመሥራት ጥረት የጋራ ነበር፤ በምሥራቃዊው ሸለቆ ላይ የነበረው ግንብም በከፊል ተንዶ ነበር፤ ካፋነታ በመባል በምሥራቃዊው ሸለቆ ላይ የነበረው ግንብም በከፊል ተንዶ ነበር፤ ካፋነታ በመባል የሚታወቀውንም ክፍል ጠገነ።

38 ስምዖን አዲዳን እንደገና ገነባት፥ አጠናከራት፥ ባለመቆለፊያ መዝጊያም አደረገባት።


ዮናታን በጠላቶቹ እጅ ወደቀ

39 ትሪፎን በእስያ ላይ ለመንገሥ፤ አክሊል ለመድፋት፥ በንጉሥ አንጥዮኩስ ላይ እጁን ለመዘርጋት ይፈልግ ነበር።

40 ዮናታን ይህን ከማድረግ እንዳያግደውና እንዳይወጋው ፈርቶ እርሱን ለመያዝና ለመግደል ይሻ ነበር፤ ተነሥቶ ወደ ቤተሳን መጣ።

41 ዮናታን ምርጥ የሆኑ አርባ ሺህ ሰዎች አስከትሎ ሊገጠመው ሄደ፤ ወደ ቤተሳንም ደረሰ፤

42 ዮናታን ከብዙ ወታደሮች ጋር መምጣቱን ትሪፎን ባየ ጊዜ በእርሱ ላይ እጁን ከመዘርጋት ተቆጠበ።

43 እንዲያውም በክብር ተቀበለውና ወደ ወዳጆቹ ሁሉ አቀረበው፤ እጅ መንሻዎችም አቀረበለት፤ ለወዳጆቹ ሁሉና ለወታደሮቹም፥ “ልክ ለእኔ እንደምትታዘዙኝ እንዲሁም ለዮናታን ታዘዙ” ሲል ትእዛዝ ሰጣቸው።

44 ዮናታንን እንዲህ አለው፦ “አሁን የሚያስፈራን ምንም ጦርነት ስለሌብን ስለምን ይህን ሁሉ ሕዝብ ታደክማለህ?

45 ስለዚህ ወደየቤታቸው እንዲሄዱ አሰናብታቸውና እንሂድ፥ ያችን ከተማና ሌሎች ምሽጐች፥ የቀሩትን ወታደሮችና የጦር አለቆች ሁሉ እሰጥሃለሁ፤ ከዚህ በኋላ እኔ ወደ ሀገሬ እመለሳለሁ፤ አመጣጤም ለዚሁ ነበር።”

46 ዮናታንም ስላመነው እርሱ እንዳለው አደረገ፤ ሠራዊቱን አሰናበተ፤ እነርሱም ወደ ይሁዳ ምድር ተመለሱ።

47 ከእርሱ ጋር ሦስት ሺህ ሰዎች አስቀረ፤ ከእነርሱ ሁለቱን ሺህ ወደ ገሊላ ላከ፤ ሺህ ሰዎች ተከተሉት።

48 ነገር ግን ዮናታን ወደ ጰጦሎማይዳ በገባ ጊዜ የዚያ አገር ነዋሪዎች በሩን ዘጉበትና ያዙት፤ ከእርሱ ጋር የገቡትንም ሰዎቹ ሁሉ በሰይፍ ገደሉዋቸው።

49 ትሪፎን የዮናታንን ሰዎች ለመግደል ወደ ገሊላና ወደ ታላቁ ሜዳ እግረኛ ወታደሮችንና ፈረሰኛ ጦሩን ላከ።

50 የዮናታን ሰዎች ዮናታን መያዙና እርሱም ሆነ ጓደኞቹ ሳይገደሉ እንዳልቀሩ ገባቸው፤ ስለዚህ እርስ በርሳቸው ተማከሩ፤ ተሰብስበበውና ለውጊያ ዝግጁዎች ሆነው ወጡ።

51 የሚከታተሏቸው ሰዎች እነርሱ ሕይወታቸውን ለማዳን የሚዋጉ መሆናቸውን አይተው ወደ ኋላ ተመለሱ።

52 ሁሉም በሰላም ወደ ይሁዳ አገር ደረሱ፤ ስለዮናታንና ስለጓደኞቹ አለቀሱ፤ በጣምም ፈሩ። የእስራኤል ሕዝብ በሙሉ ታላቅ ኀዘን አደረገ።

53 በአካባቢው ያሉ ሕዝቦች ሁሉ ሊደመስሱዋቸው ፈለጉ፤ “መሪም ሆነ ድጋፍ የላቸውም፤ ስለዚህ አሁን እንውጋቸው፤ መታሰቢያቸው ከሰዎች መካከል እንዲጠፋ እናድርግ” አሉ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች