Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

1 ነገሥት 3 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ንጉሥ ሰሎሞን ጥበብ ይሰጠው ዘንድ እግዚአብሔርን ስለ መለመኑ
( 2ዜ.መ. 1፥3-12 )

1 ሰሎሞን የግብጽን ንጉሥ ሴት ልጅ በማግባት ከንጉሡ ጋር ወዳጅነት መሠረተ፤ እርሷንም አምጥቶ ቤተ መንግሥቱን፥ የጌታን ቤትና የኢየሩሳሌምን ዙሪያ ቅጽር ሠርቶ እስኪጨርስ ድረስ በዳዊት ከተማ አኖራት።

2 በዚያን ጊዜ በጌታ ስም ቤተ መቅደሱ ገና አልተሠራም ነበር፤ ከዚህም የተነሣ በየኮረብታው መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር።

3 ሰሎሞን ጌታን ይወድ ነበር፤ የአባቱንም የዳዊትን መመሪያ ይጠብቅ ነበር፤ ይሁን እንጂ እንስሶችን እያረደ በተለያዩ ኰረብቶች ላይ መሥዋዕት ያቀርብ፥ ዕጣንም ያጥን ነበር።

4 ታላቁ መሠዊያ የሚገኘው በገባዖን ስለ ነበር አንድ ቀን ሰሎሞን መሥዋዕትን ለማቅረብ ወደዚያ ሄደ፤ ከዚህም በፊት በዚያ መሠዊያ ላይ አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል።

5 በዚያች ሌሊት ጌታ በገባዖን ለሰሎሞን በሕልም ተገለጠለትና “ምን እንድሰጥህ ትፈልጋለህ?” አለው።

6 ሰሎሞንም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አገልጋይህ የነበረው አባቴ ዳዊት ደግ፥ ታማኝና ቅን ሰው በመሆኑ ጽኑ ፍቅርህን ስታሳየው ኖረሃል፤ ዛሬም በእርሱ እግር ተተክቶ በዙፋኑ የሚቀመጥ ልጅ በመስጠት ታላቅና ጽኑ የሆነውን የማያቋርጥ ፍቅርህን ገልጠህለታል።

7 አቤቱ፥ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! እነሆ እኔ በዕድሜ አነስተኛ ነኝ፤ የአመራር ልምድም የለኝም፤ አንተ ግን በአባቴ እግር ተተክቼ እንድነግሥ ፈቃድህ ሆኖአል።

8 እነሆ እኔ የአንተ እንዲሆን በመረጥከውና ከብዛቱ የተነሣ ሊቆጠር በማይችል ሕዝብ መካከል እገኛለሁ።

9 ስለዚህ ክፉውንና በጎውን በመለየት ሕዝብህን በትክክለኛ ፍርድ ለመምራት የሚያስችለኝን ጥበብ ስጠኝ፤ ይህ ካልሆነ ግን ታላቅ ሕዝብህን እንዴት ልመራ እችላለሁ?”

10 ሰሎሞን ይህን በመጠየቁ ጌታን ደስ አሰኘው።

11 እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “ለራስህ ረጅም ዕድሜ ወይም ሀብት ለማግኘት ወይም ጠላቶችህ እንዲጠፉልህ መመኘት ሳይሆን በትክክለኛ ፍርድ ማስተዳደር የምትችልበትን ጥበብ ስለ ጠየቅህ፥

12 እነሆ የጠየቅኸውን አደርጋለሁ፤ እንዲያውም ማንም ሰው ከዚህ በፊት ካገኘውና ወደፊትም ሊያገኘው ከሚችለው የበለጠ ጥበብንና አስተዋይነትን እሰጥሃለሁ።

13 ከዚህም በላይ አንተ ያልጠየቅከውንም ሁሉ ጨምሬ እሰጥሃለሁ፤ ይኸውም በዘመንህ ማንኛውም ሌላ ንጉሥ ያላገኘውን ብልጽግናና ክብር አበዛልሃለሁ።

14 አባትህ ዳዊት እንዳደረገው በመንገዴ ብትሄድና ለእኔም ብትታዘዝ፥ ሕጌንና ትእዛዞቼንም ብትፈጽም ረጅም ዕድሜ እሰጥሃለሁ።”

15 ሰሎሞን ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ እግዚአብሔር በሕልም ተገልጦ ያነጋገረው መሆኑን ተገነዘበ፤ ከዚህ በኋላ ሰሎሞን ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ ሄደ፤ በጌታ የቃል ኪዳን ታቦት ፊት ቆሞ የሚቃጠል መሥዋዕትንና የኅብረት መሥዋዕት አቀረበ፤ ለባለሟሎቹም ሁሉ ግብዣ አደረገ።


ጥበብ የሞላበት የሰሎሞን ፍትሕ

16 አንድ ቀን ሁለት ጋለሞታዎች መጥተው በሰሎሞን ፊት ቀረቡ።

17 ከእነርሱም አንደኛይቱ እንዲህ አለች፤ “ንጉሥ ሆይ! ይህች ሴትና እኔ በአንድ ቤት አብረን ስንኖር በዚያው በምንኖርበት ቤት ወንድ ልጅ ወለድኩ።

18 እኔ በወለድኩ በሦስተኛው ቀን እርሷም ወንድ ልጅ ወለደች፤ በዚያ ቤት ውስጥ ከሁለታችን በቀር ሌላ ማንም አልነበረም።

19 ከዕለታት አንድ ቀን ሌሊት በላዩ ላይ ተኝታበት ስለ ታፈነ ልጇ ሞተ።

20 እኔ ተኝቼ ሳለሁ ሌሊት ተነሥታ ታቅፌው የተኛሁትን ልጄን ወስዳ በእርሷ አልጋ ላይ ካስተኛች በኋላ የሞተውን ልጇን አምጥታ በእኔ አልጋ ላይ በጐኔ አስተኛችው።

21 በማግስቱ ማለዳ ተነሥቼ ልጄን ለማጥባት ስዘጋጅ የሞተ ሆኖ አገኘሁት፤ ትኲር ብዬ ስመለከተው እኔ የወለድኩት ልጅ አለመሆኑን ተገነዘብኩ።”

22 ሁለተኛይቱ ሴት ግን፥ “አይደለም! በሕይወት ያለው ልጅ የእኔ ነው፤ የሞተው ግን የአንቺ ነው!” አለች። የመጀመሪያይቱ ሴት “አይደለም! የሞተው የአንቺ ልጅ ነው፤ በሕይወት ያለው ግን የእኔ ልጅ ነው!” አለች። በዚህም ዓይነት በንጉሡ ፊት ተከራከሩ።

23 ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን “አንደኛዋ ‘በሕይወት ያለው ልጅ የእኔ ነው፤ የሞተው ግን የአንቺ ነው!’ ትላለች፤ ሌላይቱ ደግሞ ‘አይደለም! የአንቺ ልጅ ሞቷል፤ የእኔ ልጅ በሕይወት ያለው ነው!’ ትላታለች አለ።”

24 ንጉሡም ሰይፍ እንዲያመጡለት አዘዘ፤ ሰይፍም አመጡለት።

25 “በሉ እንግዲህ በሕይወት ያለውን ልጅ ለሁለት ቁረጡና ለእያንዳንዷ ሴት ግማሽ አካሉን ስጡ” ሲል አዘዘ።

26 እውነተኛይቱ እናት ግን ለልጇ በመራራት አዝና፥ “ንጉሥ ሆይ! እባክህ ልጁን አትግደለው! ለእርሷ ይሰጣት!” አለች። ሌላይቱ ሴት ግን “ለእኔም ለእርሷም አይሁን! ለሁለት ይቆረጥ!” አለች።

27 ከዚህ በኋላ ሰሎሞን “ሕፃኑን አትግደሉት! እውነተኛይቱ እናት እርሷ ስለ ሆነች ለመጀመሪያይቱ ሴት ስጡአት!” ሲል አዘዘ።

28 እስራኤላውያን ይህን የፍርድ ውሳኔ በሰሙ ጊዜ ሰሎሞን የሕዝብ ጉዳዮችን በትክክለኛ ፍርድ የሚወስንበትን ጥበብ እግዚአብሔር የሰጠው መሆኑን ስለ ተገነዘቡ ታላቅ አክብሮት ሰጡት።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች