Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

1 ነገሥት 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


ዳዊት ለሰሎሞን የሰጠው የመጨረሻ መመሪያ

1 ዳዊት የሚሞትበት ወቅት በተቃረበ ጊዜ ልጁን ሰሎሞንን ጠርቶ ይህን የመጨረሻ ትእዛዝ ሰጠው፤

2 “እነሆ እኔ ሰው ሁሉ እንደሚሞት የምሞትበት ጊዜ ተቃርቧል፤ እንግዲህ በርታ! ቆራጥ ሰው ሁን፤

3 አምላክህ ጌታ እንድታደርግ የሚያዝህን ሁሉ አድርግ፤ በምትሄድበት ስፍራ ሁሉ የምታደርገው ማንኛውም ነገር እንዲከናወንልህ በሙሴ አማካይነት በተሰጠው ሕግ የተጻፉትን የእግዚአብሔርን ሕግና ትእዛዝ፥ ሥርዓትና ፈቃድ ሁሉ ጠብቅ፤

4 በዚህ ሁሉ ነገር ታዛዥ ብትሆንለት፥ ‘ዘሮችህ በጥንቃቄ ተጠብቀው ቢኖሩ፥ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው በፊቴ በቅንነት ቢመላለሱ፥ በእስራኤል ዙፋን ላይ ነግሦ የሚገዛ ዘር አላሳጣህም’ ብሎ ጌታ የነገረኝን የተስፋ ቃል ይፈጽማል።

5 “የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ የእስራኤል ሕዝብ የጦር መሪዎች ከነበሩት በኔር ልጅ አበኔርና በይቴር ልጅ ዐማሣ ላይ ያደረገውን ታስታውሳለህ፤ ሁለት በጦርነት ጊዜ ላፈሰሱት ደም በቀል በሰላም ጊዜ እነርሱን ገድሎ የወገቡን መታጠቂያ የእግሩን ጫማ በደም በክሎ በእኔ ላይ ምን እንዳደረገ ታውቃለህ።

6 እንግዲህ ባለህ ጥበብ፥ ሊፈጸም የሚገባውን ነገር አድርግ፤ ዕድሜ ጠግቦ በሰላም እንዲሞት አትፍቀድለት።

7 “ከወንድምህ ከአቤሴሎም ፊት በሸሸሁ ጊዜ የቸርነት ሥራ ስላደረጉልኝ ለገለዓዳዊው ለባርዚላይ ልጆች ግን መልካም ነገር በማድረግ ተንከባከባቸው፤ በማዕድህም ከሚመገቡት መካከል ይሁኑ።

8 “ከዚህም ጋር መረሳት የሌለበት የብንያም ክፍል በሆነችው በባሑሪም ከተማ ውስጥ የሚኖረው የጌራ ልጅ ሺምዒ አለ፤ እርሱ ወደ ማሕናይም በሄድኩበት ቀን በእኔ ላይ የስድብ ውርጅብኝ አውርዶብኛል፤ ይሁን እንጂ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ባገኘኝ ጊዜ እንደማላስገድለው በጌታ ስም ቃል ገብቼለት ነበር፤

9 አንተ ግን እርሱንም ከቅጣት ነጻ አታድርገው፤ ባለህ ጥበብ ምን መደረግ እንዳለበት አንተ ራስህ ታውቃለህ፤ በሞት የሚቀጣ መሆኑንም አትዘንጋ።”


የዳዊት መሞት

10 ዳዊት ሞተ፤ የእርሱ ከተማ በሆነችው በኢየሩሳሌምም ተቀበረ።

11 ዳዊት በኬብሮን ሰባት ዓመት፥ በኢየሩሳሌም ሠላሳ ሦስት ዓመት በድምሩ አርባ ዓመት በእስራኤል ላይ ነገሠ።

12 ሰሎሞንም በአባቱ እግር ተተክቶ ነገሠ፤ የመንግሥቱም ሥልጣን እጅግ የጸና ሆነ።


የአዶንያስ መሞት

13 የሐጊት ልጅ አዶንያስ ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ ሄደ፤ ቤርሳቤህም “ወደ እኔ የመጣኸው በሰላም ነውን?” ስትል ጠየቀችው። እርሱም “አዎን በሰላም ነው የመጣሁት” ሲል መለሰ።

14 ቀጠል አድርጎም “እኔ የምጠይቅሽ ጉዳይ አለኝ” አላት። እርሷም “ጉዳይህ ምንድነው?” አለችው።

15 አዶንያስም እንዲህ አላት፦ “ንጉሥ መሆን የሚገባኝ እኔ እንደ ነበርኩና ይህንንም በእስራኤል ምድር የሚኖር ሁሉ በተስፋ ይጠባበቅ እንደ ነበር አንቺ ራስሽ ታውቂያለሽ፤ ነገር ግን ጉዳዩ ከጌታ ስለ ተወሰነ ለእኔ መሰጠት የሚገባው መንግሥት ተላልፎ ለወንድሜ ሆኖአል።

16 አሁንም የምጠይቅሽ አንድ ጉዳይ ስላለኝ እምቢ በማለት አታሳፍሪኝ።” ቤርሳቤህም “ጉዳይህ ምንድነው?” ስትል ጠየቀችው።

17 እርሱም “ንጉሥ ሰሎሞን አንቺን እምቢ እንደማይልሽ ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ አቢሻግ ተብላ የምትጠራውን ሹኔማይት ልጃገረድ በሚስትነት እንዲድርልኝ እባክሽ አማልጅኝ” አላት።

18 እርሷም “መልካም ነው! ይህን ለንጉሡ እነግርልሃለሁ” አለችው።

19 ስለዚህም ቤርሳቤህ የአዶንያስን ጉዳይ ልትነግር ወደ ንጉሡ ገባች፤ ንጉሡም ከተቀመጠበት ተነሥቶ እናቱን እጅ በመንሣት ተቀበላት፤ እርሱም በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠ በኋላ ሌላ ዙፋን አስመጥቶ በቀኙ አስቀመጣት፤

20 እርሷም “እንድትፈጽምልኝ የምጠይቅህ አንድ ትንሽ ጉዳይ አለኝ፤ እባክህ እምቢ በማለት አታሳፍረኝ” አለችው። ንጉሡም “እናቴ ሆይ! አላሳፍርሽም፤ ጉዳዩ ምንድነው” አላት።

21 እርሷም “ወንድምህ አዶንያስ አቢሻግን ሚስት አድርጎ ያገባ ዘንድ ፍቀድለት” አለችው።

22 ንጉሡም “አቢሻግን በሚስትነት እንድድርለት ብቻ ለምን ትጠይቂኛለሽ? መንግሥቴንም ጭምር እንድለቅለት ለምን አልጠየቅሽኝም? እርሱ እኮ ታላቅ ወንድሜ ነው፤ ለምን ለካህኑ አብያታርና ለኢዮአብም ልዩ አስተያየት እንዳደርግላቸው አትጠይቂላቸውም!” አላት።

23 ከዚህ በኋላ ሰሎሞን በጌታ ስም እንዲህ ሲል ማለ፦ “አዶንያስ ይህን በማቀዱ በሕይወቱ እንዲከፈል ባላደርግ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ በበለጠም ይቅጣኝ!

24 እግዚአብሔር በአባቴ በዳዊት ዙፋን ላይ አስቀምጦ መንግሥቴን የጸና አድርጎልኛል፤ ይህን መንግሥት ለእኔና ለዘሮቼ በመስጠት ቃሉን ጠብቆአል፤ እንግዲህ አዶንያስ በዚህ በዛሬው ቀን በሞት እንደሚቀጣ በሕያው ጌታ ስም እምላለሁ!”

25 ስለዚህም አዶንያስን እንዲገድለው ንጉሥ ሰሎሞን ለዮዳሄ ልጅ ለበናያ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ በናያም ሄዶ አዶንያስን ገደለው።


የአብያታር መሳደድና የኢዮአብ በሞት መቀጣት

26 ንጉሥ ሰሎሞን ካህኑን አብያታርን፤ “ወደ ትውልድ አገርህ ወደ ዐናቶት ሂድ፤ አንተ በሞት ልትቀጣ ይገባህ ነበር፤ ነገር ግን የልዑል እግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት በአባቴ በዳዊት ፊት ትሸከም ስለ ነበርክ ከእርሱም ጋር የመከራው ሁሉ ተካፋይ ስለ ነበርክ እኔ አሁን አልገድልህም” አለው።

27 ስለዚህ ሰሎሞን አብያታርን የጌታ ካህን ሆኖ ከሚያገለግልበት የክህነት ሥልጣን ሽሮ አባረረው፤ በዚህም ዓይነት ጌታ በሴሎ ስለ ካህኑ ዔሊና ስለ ትውልዱ የተናገረው ቃል ተፈጸመ።

28 በአንድ በኩል የአዶንያስ ደጋፊ፥ በሌላ በኩል ደግሞ የአቤሴሎም ተቃዋሚ የሆነው ኢዮአብ የተፈጸመውን ነገር ሁሉ ሰማ፤ ስለዚህም ሸሽቶ ወደ ጌታ ድንኳን ሄደ፤ በዚያም የመሠዊያውን ቀንዶች ይዞ ተማጠነ።

29 ኢዮአብ ወደ ጌታ ድንኳን ሸሽቶ መሄዱንና በመሠዊያው አጠገብ መገኘቱን ሰሎሞን በሰማ ጊዜ፥ ኢዮአብን እንዲገድለው ለበናያ ትእዛዝ አስተላለፈ።

30 እርሱም ወደ ጌታ ድንኳን ሄዶ ኢዮአብን “ከዚህ ድንኳን እንድትወጣ ንጉሡ አዞሃል” አለው። ኢዮአብ ግን “አልወጣም! እዚሁ እሞታለሁ!” አለ። በናያም ተመልሶ ኢዮአብ ያለውን ለንጉሡ ነገረው።

31 ሰሎሞንም በናያን እንዲህ አለው፤ “ኢዮአብ እንዳለህ ግደለውና ቅበረው፤ በዚህ አኳኋን ኢዮአብ ካፈሰሰው ንጹሕ ደም በደል የእኔንና የአባቴን ቤት የነጻን አድርገን።

32 አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ኢዮአብ ስለ ገደላቸው ስለ እነዚያ ሰዎች ደም ጌታ ኢዮአብን ይቀጣዋል፤ ኢዮአብ ከእርሱ የተሻሉትን ሁለት ንጹሓን ሰዎች ገድሎአል፤ እነርሱም የእስራኤል ጦር አዛዥ አበኔርና የይሁዳ ጦር አዛዥ ዐማሣ ነበሩ።

33 ኢዮአብ እነዚህን ሰዎች በመግደሉ በእርሱ ላይ የተፈጸመበት ቅጣት በእርሱና በዘሮቹ ላይ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኑር፤ በዙፋኑ ላይ ለሚቀመጡት ለዳዊት ዘሮች ግን የጌታ ሰላም ለዘለዓለም አይለያቸው።”

34 ስለዚህ በናያ በታዘዘው መሠረት ኢዮአብን ገደለው፤ በቤቱም አጠገብ በሚገኘው በረሓ ተቀበረ።

35 ንጉሥ ሰሎሞን በኢዮአብ ፈንታ በናያን የሠራዊቱ አዛዥ፥ በአብያታርም ፈንታ ሳዶቅን ካህን አድርጎ ሾመ።


የሺምዒ መሞት

36 ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን ሽምዒን አስጠርቶ እንዲህ ሲል አዘዘው፤ “በዚህ በኢየሩሳሌም የራስህን መኖሪያ ቤት ሠርተህ ተቀመጥ፤ ከዚያ ወደየትም አትሂድ፤

37 ከከተማይቱ ወጥተህ የቄድሮንን ወንዝ ተሻግረህ ብትገኝ በእርግጥ ትሞታለህ፤ ለደምህም ተጠያቂ ራስህ ነህ።”

38 ሺምዒም “ንጉሥ ሆይ! ውሳኔህ ትክክል ነው፤ እኔ አገልጋይህ አንተ ጌታዬ እንዳልከው አደርጋለሁ” ሲል መለሰ፤ ስለዚህ በኢየሩሳሌም ብዙ ጊዜ ተቀመጠ።

39 ከሦስት ዓመት በኋላ ግን ሁለቱ የሺምዒ አገልጋዮች የማዕካ ልጅ ወደ ሆነው አኪሽ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ጋት ንጉሥ ኰብልለው ሄዱ፤ ሺምዒም ባርያዎቹ በጋት መኖራቸው ተነገረው፤

40 አህያውን ጭኖ እነርሱን ለማግኘት በጋት ወደሚኖረው ወደ ንጉሥ አኪሽ ሄደ፤ እነርሱንም በዚያ ስላገኛቸው ወደ ቤቱ መልሶ አመጣቸው።

41 ሰሎሞን ሺምዒ ከኢየሩሳሌም ወደ ጋት ሄዶ መመለሱን ሰማ።

42 ንጉሡም ሽምዒን አስጠርቶ “ከኢየሩሳሌም እንዳትወጣ በጌታ ስም አስምዬህ አልነበረምን? ወጥተህ ብትገኝ ግን በእርግጥ እንደምትሞት አስጠንቅቄህ አልነበረምን? በዚህስ ተስማምተህ ትእዛዜን እንደምትፈጽም ቃል ገብተህልኝ አልነበረምን?” አለው።

43 “ታዲያ፥ በጌታ ስም ከማልክ በኋላ ለምን መሐላውን አልጠበቅህም? ያዘዝኩህን ትእዛዝስ ለምን አላከበርክም?

44 በአባቴ በንጉሥ ዳዊት ላይ የፈጸምከውን በደል ሁሉ በደንብ ታውቃለህ፤ አንተ ስላደረግኸው ክፉ ነገር ጌታ ራሱ ይቀጣሃል፤

45 እኔን ንጉሥ ሰለሞንን ግን ጌታ ይባርከኛል፤ የዳዊት መንግሥትም ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል።”

46 ከዚህም በኋላ ለዮዳሄ ልጅ ለበናያ ሺምዒን እንዲገድል ትእዛዝ አስተላለፈ፤ በናያም ሄዶ ሺምዒን ገደለው፤ በዚህም ዓይነት መንግሥቱ በሰሎሞን እጅ የጸና ሆነ።

ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች