1 ነገሥት 18 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ኤልያስና ሐሰተኞቹ የባዓል ነቢያት 1 ከብዙ ጊዜ በኋላ በሦስተኛው ዓመት ጌታ ኤልያስን “ሄደህ ራስህን ለንጉሥ አክዓብ ግለጥለት፤ እኔም በምድር ላይ ዝናብን አዘንባለሁ” አለው። 2 ኤልያስም በታዘዘው መሠረት ወደ አክዓብ ሄደ፤ በዚህ ጊዜ በሰማርያ ረሀብ እጅግ ጸንቶ ነበር። 3 ስለዚህም ንጉሥ አክዓብ የቤተ መንግሥቱ ኀላፊ የሆነውን አብድዩን ጠራ፤ አብድዩ ጌታን የሚፈራ መንፈሳዊ ሰው ነው። 4 ኤልዛቤል የጌታን ነቢያት ታስገድል በነበረችበትም ጊዜ አብድዩ አንድ መቶ የሚሆኑትን የእግዚአብሔርን ነቢያት ከሁለት ከፍሎ ኀምሳ፥ ኀምሳውን በዋሻዎች ከሸሸጋቸው በኋላ እህልና ውሃ በማቅረብ ይመግባቸው ነበር። 5 አክዓብ አብድዩን “ፈረሶችንና በቅሎዎችን ከሞት የምናድንበት በቂ ሣር እናገኝ እንደሆን በምድሪቱ ወደሚገኘው ምንጭና ወንዝ እስቲ ሂድና እይ፤ ምናልባት እንስሶቻችንን ከሞት ማዳን እንችል ይሆናል” አለው። 6 እያንዳንዳቸው በአገሪቱ ወደየትኛው ክፍል ሄደው መፈለግ እንዳለባቸው ከተስማሙ በኋላ አክዓብና አብድዩ ለየብቻቸው በሁለት አቅጣጫ ተሰማሩ። 7 አብድዩ በሚሄድበት መንገድ ላይ ሳለ በድንገት ኤልያስን አገኘው፤ ኤልያስ መሆኑንም ስላወቀ በግንባሩ ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ ከነሣው በኋላ “ጌታዬ ኤልያስ! በእውነት አንተ ነህን?” ሲል ጠየቀው። 8 ኤልያስም “አዎ! እኔ ነኝ፤ እዚህ መሆኔን ሄደህ ለጌታህ ንገረው” ሲል መለሰለት። 9 አብድዩም እንዲህ አለው፤ “ንጉሥ አክዓብ እኔን ባርያህን ይገድለኝ ዘንድ በእጁ አሳልፈህ የምትሰጠኝ ምን በደል ሠርቼ ነው? 10 ንጉሡ አንተን ለማግኘት ፈልጎ በዓለም ላይ መልእክተኛ ያልላከበት አገር እንደሌለ በአምላክህ በሕያው ጌታ ስም እምላለሁ፤ የአንድ አገር መሪ አንተ በአገሩ ውስጥ አለመኖርክን ባስታወቀው ቍጥር ንጉሥ አክዓብ የአንተን አለመኖር በመሐላ እንዲያረጋግጥለት ጠይቆአል። 11 አሁን አንተ ግን ኤልያስ ተገኝቶአል ብለህ ለጌታህ ንገር ትለኛለህ። 12 እኔ ከዚህ እንደ ሄድኩ ወዲያውኑ የጌታ መንፈስ አንተን ወዳልታወቀ ቦታ ቢወስድህ እኔ ምን ይበጀኛል? አንተ በዚህ ቦታ መኖርኽን ለአክዓብ ነግሬው ሳያገኝህ ቢቀር እርሱ እኔን በሞት ይቀጣኛል፤ ከልጅነቴ ጀምሬ ጌታን የምፈራ ሰው መሆኔን አስታውስ። 13 ደግሞስ ኤልዛቤል የጌታን ነቢያት ስታስገድል በነበረችበት ጊዜ አንድ መቶ የሚሆኑትን ነቢያት ከሁለት በመክፈል ኀምሳ ኀምሳውን በዋሻዎች ውስጥ ሸሽጌ እህልና ውሃ በማቅረብ ስመግባቸው መኖሬን አልሰማህምን? 14 ታዲያ፥ አሁን አንተ እዚህ መሆንህን ሄደህ ለንጉሥ አክዓብ ንገር ትለኛለህን? ይህን ባደርግ ንጉሡ ይገድለኛል!” 15 ኤልያስም “ዛሬ እኔ ለንጉሡ ራሴን እንደምገልጥለት በማገለግለውና ሁሉን ቻይ በሆነው በጌታ ስም ቃል እገባልሃለሁ!” ሲል መለሰ። 16 ከዚህ በኋላ አብድዩ ሄዶ ለንጉሥ አክዓብ ነገረው፤ አክዓብም ተነሥቶ ኤልያስን ለመገናኘት ሄደ። 17 አክዓብ ኤልያስን ባየው ጊዜም “በእስራኤል ላይ ይህን ከባድ ችግር ያመጣህ አንተ ለካ እዚህ ነህን?” አለው። 18 ኤልያስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “የእግዚአብሔርን ትእዛዞች በመጣስ ባዓል ተብሎ ለሚጠራው የባዕድ አምላክ ምስሎች በመስገድ ችግር የምታመጡ አንተና የአባትህ ቤተሰብ ናችሁ እንጂ እኔ በእስራኤል ላይ ችግር የማመጣ አይደለሁም! 19 ይልቅስ አሁን እስራኤላውያንን ሁሉ እንዳገኛቸው በቀርሜሎስ ተራራ ሰብስብልኝ፤ በንግሥት ኤልዛቤል ማእድ የሚቀለቡትን አራት መቶ ኀምሳ የባዓል ነቢያትንና አራት መቶ የአሼራ ነቢያትን ጭምር ይዘህ ና።” 20 ስለዚህም አክዓብ ለእስራኤላውያን ሁሉና ለነቢያት በሙሉ ጥሪ አድርጎ በቀርሜሎስ ተራራ እንዲሰበሰቡ አስደረገ። 21 ኤልያስም ወጥቶ ለሰዎቹ፦ “እስከ መቼ ድረስ በሁለት ልብ ስታወላውሉ ትኖራላችሁ? እንግዲህ ጌታ እውነተኛ አምላክ ከሆነ እርሱን አምልኩ! ወይም ባዓል እውነተኛ አምላክ ከሆነ እርሱኑ አምልኩ!” አላቸው፤ ሕዝቡ ግን አንዲት ቃል እንኳ አልመለሱም። 22 ከዚህ በኋላ ኤልያስ እንዲህ አለ፦ “ከጌታ ነቢያት የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ፤ አራት መቶ ኀምሳ የባዓል ነቢያት ግን እነሆ በዚህ አሉ፤ 23 እንግዲህ ሁለት ኰርማዎችን አምጡና የባዓል ነቢያት አንዱን ወስደው ይረዱት፤ ሥጋውንም ቆራርጠው እንጨት በመረብረብ በዚያ ላይ ያኑሩት፤ ነገር ግን በእሳት አያቀጣጥሉት፤ እኔም ሁለተኛውን ኰርማ ወስጄ እንደዚሁ አደርጋለሁ። 24 ከዚህ በኋላ የባዓል ነቢያት ወደ አምላካቸው ይጸልዩ፤ እኔም ወደ ጌታ እጸልያለሁ፤ እሳትን ወደ መሥዋዕቱ በመላክ መልስ የሚሰጥ እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው።” ሕዝቡም ድምፁን ከፍ አድርጎ በዚህ ሐሳብ መስማማቱን ገለጠ። 25 ከዚህ በኋላ ኤልያስ የበዓልን ነቢያት “እናንተ ብዙ ስለ ሆናችሁ በመጀመሪያ አንዱን ኰርማ መርጣችሁ በማረድ ወደ አምላካችሁ ጸልዩ፤ ነገር ግን እንጨቱን በእሳት አታቀጣጥሉ” አላቸው። 26 እነርሱም የመጣላቸውን ኰርማ ወስደው ለመሥዋዕት አዘጋጅተው እስከ እኩለ ቀን ድረስ ወደ ባዓል ጸለዩ። “ባዓል ሆይ! እባክህ ስማን!” እያሉም ጮኹ። በሠሩትም መሠዊያ እየዘለሉ ዞሩ፤ ነገር ግን ምንም መልስ አላገኙም። 27 እኩለ ቀን ሲሆን ኤልያስ “ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ጸልዩ! እርሱ አምላክ አይደለም እንዴ እርሱ በሐሳብ ተውጦ ይሆናል! ወይም ራሱን ያዝናና ይሆናል! ወይም ወደ ሩቅ አገር ሄዶ ይሆናል! ወይም ተኝቶ ያንቀላፋ ይሆናልና እንዲነቃ ቀስቅሱት!” እያለ ያፌዝባቸው ጀመር። 28 ስለዚህም የሐሰት ነቢያቱ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እየጸለዩ በሥርዓታቸው መሠረት ደማቸው እስኪፈስ ድረስ በቢላዋና በጩቤ ሰውነታቸውን ያቆስሉ ነበር። 29 እኩለ ቀን ካለፈም በኋላ የሠርክ መሥዋዕት እስከሚቀርብበት ጊዜ ድረስ እየተራወጡ ይቀባጥሩ ነበር፤ ይሁን እንጂ ምንም መልስ አላገኙም፤ ድምፅም አልተሰማም። 30 ከዚህ በኋላ ኤልያስ ሰዎቹን “ወደ እኔ ቅረቡ” አላቸው፤ ሁሉም በዙሪያው ተሰበሰቡ፤ እርሱም ፈርሶ የነበረውን የጌታ መሠዊያ በማደስ ሠራው። 31 ጌታ ከዚያ በፊት “እስራኤል” ብሎ ከሰየመው ከያዕቆብ በተወለዱት በዐሥራ ሁለቱ ነገዶች ስም ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች ወሰደ። 32 እነዚህንም ድንጋዮች ረብርቦ በጌታ ስም መሠዊያ ሠራ፤ በዙሪያውም ዐሥራ አራት ሊትር ውሃ የሚይዝ ጉድጓድ ማሰ። 33 እንጨቱንም በመሠዊያው ላይ በመረብረብ ኰርማውን በብልት በብልቱ ቆራርጦ በእንጨቱ ላይ ካኖረ በኋላ፥ 34 “በአራት ጋን ውሃ ሞልታችሁ በመሥዋዕቱና በእንጨቱ ላይ አፍስሱት!” አላቸው፤ እነርሱም እንዲሁ አደረጉ፤ “አሁንም ጨምሩበት!” አላቸው፤ እነርሱም እንዲሁ አደረጉ፤ እርሱም “አሁንም እንደገና አንድ ጊዜ ጨምሩ!” አላቸው፤ እነርሱም እንዲሁ አደረጉ። 35 ውሃውም በመሠዊያው ዙሪያ ፈሰሰ፤ ጉድጓዱንም ሞላው። 36 ከቀትር በኋላ የሠርክ መሥዋዕት በሚቀርብበት ሰዓት ነቢዩ ኤልያስ ወደ መሠዊያው ቀርቦ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “የአብርሃም፥ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ጌታ ሆይ! አንተ የእስራኤል አምላክ መሆንክን፥ እኔም የአንተ አገልጋይ መሆኔን፥ እኔም ይህን ሁሉ ያደረግኹት በቃልህ መሠረት መሆኑን አንተ ራስህ ግለጥ፤ 37 አምላኬ ሆይ! ይህ ሕዝብ አንተ እውነተኛ አምላክ መሆንህንና ወደ አንተም ያቀረብከው አንተ ራስህ መሆንህን እንዲያውቅ እባክህ መልስ ስጠኝ፤ አምላክ ሆይ፥ ስማኝ!” 38 ከዚህ በኋላ ጌታ እሳትን ላከ፤ ያም እሳት መሥዋዕቱን፥ እንጨቱንና ድንጋዩን አቃጠለ፤ ምድሩንም ለበለበ፤ በጉድጓዱ የነበረውንም ውሃ አደረቀ፤ 39 ሰዎቹም ይህን ባዩ ጊዜ በግንባራቸው መሬት ላይ ተደፍተው በመደነቅ “ጌታ አምላክ ነው! እውነተኛ አምላክ እርሱ ብቻ ነው!” አሉ። 40 ኤልያስም “የባዓልን ነቢያት ያዙ፤ አንድም ሰው እንዳያመልጥ!” ሲል አዘዘ፤ሕዝቡም በሙሉ ያዛቸው፤ ኤልያስም ወደ ቂሾን ወንዝ እየመራ ወስዶ በዚያ ሁሉንም ገደላቸው። የድርቁ ዘመን ማብቃት 41 ከዚህ በኋላ ኤልያስ ንጉሥ አክዓብን “እንግዲህ ሄደህ እህልና ውሃ ቅመስ፤ እኔ አሁን የከባድ ዝናም ነጐድጓድ ድምፅ መቃረቡን እየሰማሁ ነው” አለው። 42 አክዓብ እህልና ውሃ ለመቅመስ ሲሄድ፥ ኤልያስ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ወጣ፤ እዚያም በሁለቱ ጉልበቶቹ መካከል ራሱን ወደ መሬት ደፋ። 43 አገልጋዩን፥ “ሂድና ወደ ባሕሩ አቅጣጫ ተመልከት!” አለው። አገልጋዩም ሄዶ ሲመለስ “ምንም ነገር አይታየኝም” አለው፤ አገልጋዩ እየተመላለሰ ያይ ዘንድ ኤልያስ ሰባት ጊዜ አዘዘው። 44 በሰባተኛውም ጊዜ አገልጋዩ ተመልሶ “ከአንድ ሰው መዳፍ የማትበልጥ ትንሽ ደመና ከባሕር ስትወጣ አየሁ” አለው። ኤልያስም “ወደ ንጉሥ አክዓብ ሂድና ‘ዝናቡ ሳያቋርጥህ በፍጥነት ወደ ሠረገላህ ገብተህ ወደ ቤትህ ተመልሰህ ሂድ’ ብለህ ንገረው” ሲል አዘዘው። 45 ከጥቂት ጊዜም በኋላ ሰማዩ በጥቁር ደመና ተሸፈነ፤ ነፋሱም ይነፍስ፥ ብርቱ ዝናብም ይዘንብ ጀመረ፤ ንጉሥ አክዓብም በሠረገላው ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ፤ 46 የጌታም ኃይል በኤልያስ ላይ ወረደ፤ ኤልያስም ልብሱን በወገቡ ዙሪያ ጠበቅ አድርጎ በመታጠቅ እስከ ኢይዝራኤል መግቢያ በር ድረስ በአክዓብ ፊት ቀድሞ ይሮጥ ነበር። |