ሕዝቅኤል 39 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የጎግ መሸነፍ 1 “አንተም የሰው ልጅ ሆይ! በጎግ ላይ ትንቢትን ተናገር እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሮስ የሞሣሕና የቶቤል አለቃ ጎግ ሆይ! እነሆ እኔ በአንተ ላይ ነኝ፤ 2 እሰበስብሃለሁ፤ እመራሃለሁ፤ ከሰሜንም ዳርቻ አወጣሃለሁ፥ ወደ እስራኤልም ተራሮች እወስድሃለሁ። 3 ከግራ እጅህም ቀስትህን አስጥልሃለሁ፤ ከቀኝ እጅህም ፍላጾችህን አስረግፍሃለሁ፤ በእስራኤልም ተራሮች ላይ እጥልሃለሁ። 4 አንተና ጭፍሮችህ ሁሉ፥ ከአንተም ጋር ያሉ ሕዝብ በምድረ በዳ ፊት ትወድቃላችሁ፤ ለሚናጠቁ ወፎች ሁሉና ለምድር አራዊትም መብል አድርጌ እሰጥሃለሁ። 5 አንተ በሜዳ ፊት ላይ ትወድቃለህ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 6 በማጎግም ላይ፥ በሰላምም በደሴቶች በሚቀመጡ ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 7 ቅዱሱም ስሜ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ይታወቃል፤ ቅዱሱንም ስሜን ከእንግዲህ ወዲህ አላረክስም፤ አሕዛብም የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር፥ እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 8 እነሆ ይመጣል፤ እንደሚሆንም ታውቃላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ያልሁት ቀን ይህ ነው። 9 በእስራኤልም ከተሞች የሚኖሩ ይወጣሉ፤ የጦር መሣሪያዎችንም በእሳት ያቃጥላሉ፤ አላባሽ አግሬ ጋሻንና ጋሻን፥ ቀስትንና ፍላጻዎችን፥ የእጅ በትሮችንና ጦርንም ያቃጥላሉ፤ ሰባት ዓመት በእሳት ያቃጥሉአቸዋል። 10 እንጨትን ከሜዳ አይወስዱም፤ ከዱርም አይቈርጡም፤ ነገር ግን የጦር መሣሪያን በእሳት ያነድዳሉ፤ የገፈፉአቸውንም ይገፍፋሉ፤ የበዘበዙአቸውንም ይበዘብዛሉ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የጎግ መቃብር 11 “በዚያም ቀን በእስራኤል ዘንድ በባሕር ምሥራቅ የሚያልፉበትን ሸለቆ፥ የመቃብርን ስፍራ ለጎግ እሰጣለሁ፤ የሚያልፉትንም ይከለክላል፤ በዚያም ጎግንና ሠራዊቱን ሁሉ ይቀብራሉ፤ የሸለቆውንም ስም የጎግ መቃብር ብለው ይጠሩታል። 12 ምድርንም ያነደዱ የእስራኤል ወገኖች ሰባት ወር መቃብር እየቈፈሩ ይቀብሯቸዋል፤ 13 የምድሩም ሕዝብ ሁሉ ይቀብሯቸዋል፤ እኔም በምመሰገንበት ቀን ለክብር ይሆንላቸዋል ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 14 ምድርንም ለማጽዳት በምድሩ ላይ ወድቀው የቀሩትን የሚቀብሩ፥ ዘወትር በምድሩ ላይ የሚዞሩትን ሰዎች ይቀጥራሉ፤ ከሰባት ወርም በኋላ ይመረምራሉ። 15 በምድርም የሚዞሩት ያልፋሉ፤ የሰውንም አጥንት ቢያዩ፥ ቀባሪዎች በጎግ መቃብር ሸለቆ እስኪቀብሩት ድረስ ምልክት ያኖሩበታል። 16 ደግሞም የከተማዪቱ ስም የመቃብር ቦታ ይባላል። እንዲሁ ምድሪቱን ያጸዳሉ። 17 “አንተም የሰው ልጅ ሆይ! ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለሚበርሩ ወፎች ሁሉና ለምድር አራዊት ሁሉ እንዲህ በላቸው፦ ኑ፤ ተከማቹ፤ ሥጋንም ትበሉ ዘንድ፥ ደምንም ትጠጡ ዘንድ በእስራኤል ተራሮች ላይ ወደማርድላችሁ መሥዋዕት፥ እርሱም ታላቅ መሥዋዕት፥ ከየሰፍራው ሁሉ ተሰብሰቡ። 18 የኀያላኑን ሥጋ ትበላላችሁ፤ የምድርንም አለቆች፥ የአውራ ፍየሎችንና የአውራ በጎችን፥ የወይፈኖችንና፥ የባሳንን ፍሪዳዎች ሁሉ፥ ደም ትጠጣላችሁ። 19 እኔም ከማርድላችሁ መሥዋዕት እስክትጠግቡ ድረስ ጮማን ትበላላችሁ፤ እስክትሰክሩም ድረስ ደምን ትጠጣላችሁ። 20 ከማዕዴም ከፈረሶችና ከፈረሰኞች፥ ከኀያላንና ከሰልፈኞች ሁሉ ሥጋን ትጠግባላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የእስራኤል እንደ ገና መቋቋም 21 “ክብሬንም እሰጣችኋለሁ፤ አሕዛብም ሁሉ ያደረግሁትን ፍርዴን፥ በላያቸውም ያኖርኋትን እጄን ያያሉ። 22 ከዚች ቀን ጀምሮ ለዘለዓለም የእስራኤል ቤት እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 23 አሕዛብም የእስራኤል ቤት በኀጢአታቸው ምክንያት እንደ ተማረኩ ያውቃሉ፤ ስለ ከዱኝ እኔም ፊቴን ከእነርሱ ስለ መለስሁ፥ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፌ ሰጠኋቸው፥ እነርሱም ሁሉ በሰይፍ ወደቁ። 24 እንደ ርኵሰታቸውም እንደ መተላለፋቸውም መጠን አደረግሁባቸው፤ ፊቴንም ከእነርሱ መለስሁ። 25 “ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አሁን የያዕቆብን ምርኮ እመልሳለሁ፤ ለእስራኤልም ቤት ሁሉ እራራለሁ፤ ስለ ቅዱስ ስሜም እቀናለሁ። 26 በምድራቸው ተዘልለው በተቀመጡ ጊዜ እፍረታቸውንና የበደሉኝን በደላቸውን ሁሉ ይሸከማሉ፤ የሚያስፈራቸውም የለም። 27 ከአሕዛብም ዘንድ በመለስኋቸው ጊዜ፥ ከአሕዛብም ሀገሮች በሰበሰብኋቸው ጊዜ፥ በብዙ አሕዛብም ፊት በተቀደስሁባቸው ጊዜ፥ 28 እኔም ወደ አሕዛብ አስማርኬአቸዋለሁና፥ ወደ ገዛ ምድራቸውም ሰብስቤአቸዋለሁና እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ በዚያም ከእነርሱ አንድ ሰው ከእንግዲህ ወዲያ አላስቀርም፤ 29 ፊቴንም ከእነርሱ ከእንግዲህ ወዲህ አልመልስም፤ መዓቴን በእስራኤል ቤት ላይ አፍስሻለሁና፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |