ሕዝቅኤል 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የእግዚአብሔር ዙፋን 1 በሠላሳኛው ዓመት በአራተኛው ወር ከወሩም በአምስተኛው ቀን በኮቦር ወንዝ በምርኮኞች መካከል ሳለሁ ሰማያት ተከፈቱ፤ የእግዚአብሔርንም ራእይ አየሁ። 2 ንጉሡ ዮአኪን በተማረከ በአምስተኛው ዓመት፥ ከወሩም በአምስተኛው ቀን፥ 3 የእግዚአብሔር ቃል በከለዳውያን ሀገር በኮቦር ወንዝ ላይ ወደ ቡዝ ልጅ ወደ ካህኑ ወደ ሕዝቅኤል መጣ። የእግዚአብሔርም እጅ በዚያ በእኔ ላይ ሆነች፤ 4 እኔም አየሁ፤ እነሆም ከሰሜን በኩል ዐውሎ ነፋስና ታላቅ ደመና፥ የሚበርቅም እሳት መጣ፤ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ፤ በመካከልም በእሳቱ ውስጥ የሚብለጨለጭ ነገር ነበረ። 5 ከመካከልም የአራት እንስሶች አምሳያ ወጣ። መልካቸውም እንደዚህ ነበረ፤ ሰውም ይመስሉ ነበረ። 6 ለእያንዳንዱም አራት አራት ፊት፥ ለእያንዳንዱም አራት አራት ክንፍ ነበሩት። 7 እግሮቻቸውም ቀጥ ያሉ ነበሩ፤ የእግራቸው ሰኰና እንደ ላም እግር ሰኰና ነበረ፤ እንደ ተወለወለ ናስም ይብለጨለጭ ነበር። 8 በክንፎቻቸውም በታች በእየአራቱ ጐድናቸው የሰው እጅ ነበረ፤ ለአራቱም እንደዚህ ያሉ ፊትና ክንፍ ነበሩአቸው። 9 የሁሉም ክንፎቻቸው አንዱ ከአንዱ ጋር የተያያዘ ነው፤ ሲሄዱም ወዲያና ወዲህ ሳይሉ አቅንተው ይሄዳሉ፤ አንዱም አንዱም ወደፊቱ ይሄዳል። 10 የፊታቸው አምሳያ እንደዚህ ነው፦ ለአራቱ ሁሉ በቀኛቸው የሰው ፊትና የአንበሳ ፊት አላቸው፤ ለአራቱም ሁሉ በግራቸው የእንስሳ ፊትና የንስር ፊት አላቸው። 11 ክንፋቸውም በላይ ተዘርግቶ ነበር፤ የእያንዳንዱም ሁለት ሁለት ክንፋቸው የተያያዙ ነበሩ፤ ሁለት ሁለቱም ገላቸውን ይከድኑ ነበር። 12 እያንዳንዱም ወደ ፊት ቀጥ ብሎ ይሄድ ነበር፤ መንፈስም ወደሚሄድበት ሁሉ ይሄዱ ነበር፤ ሲሄዱም ወዲያና ወዲህ አይሉም ነበር። 13 በእንስሶቹም መካከል እንደሚነድድ የእሳት ፍም ያለ አምሳያ ነበረ፤ በእንስሶቹ መካከል ወዲህና ወዲያ የሚሄድ እንደ ፋና ያለ አምሳያ ነበረ፤ ለእሳቱም ፀዳል ነበረው፤ ከእሳቱም መብረቅ ይወጣ ነበር። 14 እንስሶቹም እንደ መብረቅ አምሳያ ይሮጡና ይመለሱ ነበር። 15 ስመለከትም፥ እነሆ በአራቱ እንስሶች አጠገብ በምድር ላይ አንድ መንኰራኵር አየሁ። 16 የመንኰራኵሩም መልክ እንደ ቢረሌ ነበረ፤ አራቱም አንድ አምሳያ ነበሩ፤ ሥራቸውም በመንኰራኵር ውስጥ እንዳለ መንኰራኵር ነበረ። 17 በእየአራቱም ጐድናቸው ይሄዱ ነበር፤ ሲሄዱም ጀርባቸውን አይመልሱም ነበር። ከፍ ከፍ ያሉም ነበሩ። 18 በአራቱ ዙሪያ ሁሉ ዐይኖችን የተመላ ጀርባቸውን አየሁ፤ 19 በሄዱም ጊዜ ሠረገላዎች ከእነርሱ ጋር ይሄዳሉ። እንስሶቹም ከምድር ሲነሡ መንኰራኵሮቹም ከእነርሱ ጋር ይነሣሉ። 20 ደመና ባለበት በዚያ መንፈስ አለ፤ እንስሶቹ ይሄዳሉ፤ ከእነርሱም ጋር መንኰራኵሮቹ ይነሣሉ፤ የሕይወት መንፈስ በመንኰራኵሮች አለና። 21 በሄዱም ጊዜ ይሄዳሉ፤ በቆሙም ጊዜ ይቆማሉ፤ በእነዚያ መንኰራኵሮች ውስጥ የሕይወት መንፈስ አለና ከምድር በተነሡ ጊዜ መንኰራኵሮቹ ከእነርሱ ጋር ይነሣሉ። 22 በእነዚያ እንስሶች ራስ ላይ ያለው መልክ ከላይ በክንፎቻቸው ላይ የተዘረጋ የበረድ መልክ እንዳለበት ጠፈር ነው፤ 23 ከጠፈሩም በታች ክንፎቻቸው እርስ በርሳቸው ተቃንተው ነበር፤ ለእያንዳንዱም ገላውን የሚከድኑ ሁለት ሁለት ክንፎች ነበሩት። 24 ሲሄዱም የክንፎቻቸው ድምፅ እንደ ብዙ ውኃ ድምፅ፥ ሁሉን እንደሚችል የአምላክም ድምፅ፥ እንደ ታላቅ ሠራዊትም ድምፅ ሆኖ ሰማሁ፤ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ይሰበስቡ ነበር። 25 በራሳቸውም ላይ ካለው ጠፈር በላይ ድምፅ ተሰማ፤ ሲቆሙም ክንፎቻቸውን ይሰበስቡ ነበር። 26 በራሳቸውም በላይ ከአለው ጠፈር በላይ የሰንፔር ድንጋይ የሚመስል የዙፋን አምሳያ ነበረ፤ በዙፋኑም አምሳያ ላይ እንደ ሰው መልክ አምሳያ ነበረ። 27 ከወገቡም አምሳያ ወደ ላይ የሚብለጨለጭ የወርቅ አምሳያ አየሁ፤ ከወገቡም አምሳያ ወደ ታች እንደ እሳት አምሳያ አየሁ፤ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ። 28 በዝናብ ቀን በደመና ውስጥ እንደ አለ ቀስተ ደመና አምሳያ፥ እንዲሁ በዙሪያው ያለ ፀዳል አምሳያ ነበረ። የእግዚአብሔር ክብር ምሳሌ መልክ ይህ ነበረ። በአየሁም ጊዜ በግንባሬ ተደፋሁ። የሚናገርንም ድምፅ ሰማሁ። |