Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ዘሌዋውያን 19 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ልዩ ልዩ ሕግጋት

1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤

2 “ለመላው የእስራኤል ሕዝብ ጉባኤ እንዲህ ብለህ ተናገራቸው፤ ‘እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ።

3 “ ‘ከእናንተ እያንዳንዱ እናቱንና አባቱን ያክብር፤ ሰንበታቴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።

4 “ ‘ወደ ጣዖታት ዘወር አትበሉ፤ ወይም ከቀለጠ ብረት ለራሳችሁ አማልክት አትሥሩ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።

5 “ ‘የኅብረት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በምታቀርቡበት ጊዜ፣ መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት እንዲያገኝላችሁ አድርጋችሁ አቅርቡ።

6 መሥዋዕቱም ባቀረባችሁት ዕለት ወይም በማግስቱ ይበላ፤ እስከ ሦስተኛው ቀን የተረፈ ማንኛውም ነገር ይቃጠል።

7 በሦስተኛውም ቀን ቢበላ ርኩስ ነው፤ ተቀባይነትም የለውም።

8 ከመሥዋዕቱ የሚበላ ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር የተቀደሰውን ነገር አርክሷልና ይጠየቅበታል፤ ያም ሰው ከወገኑ ተለይቶ ይጥፋ።

9 “ ‘የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ፣ በዕርሻችሁ ዳርና ዳር ያለውን አትጨዱ፤ ቃርሚያውንም አትልቀሙ።

10 የወይንህን ዕርሻ አትቃርም፤ የወደቀውንም አትልቀም፤ ለድኾችና ለመጻተኞች ተውላቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።

11 “ ‘አትስረቁ። “ ‘አትዋሹ። “ ‘ከእናንተ አንዱ ሌላውን አያታልል።

12 “ ‘በስሜ በሐሰት አትማሉ፤ በዚህም የአምላካችሁን ስም አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

13 “ ‘ባልንጀራህን አታጭበርብር፤ አትቀማውም። “ ‘የሙያተኛውን ደመወዝ ሳትከፍል አታሳድር።

14 “ ‘ደንቈሮውን አትርገም፤ በዐይነ ስውሩም ፊት ዕንቅፋት አታኑር፤ ነገር ግን አምላክህን ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

15 “ ‘ፍርድ አታዛቡ፤ ለድኻው አታድላለት፤ ለትልቁም ሰው ልዩ አክብሮት አትስጥ፤ ለብርቱው አታድላ፤ ነገር ግን ለባልንጀራህ በጽድቅ ፍረድ።

16 “ ‘በሕዝብህ መካከል ሐሜት አትንዛ። “ ‘የባልንጀራህን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውንም ነገር አታድርግ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

17 “ ‘ወንድምህን በልብህ አትጥላው፤ የበደሉ ተካፋይ እንዳትሆን ባልንጀራህን በግልጽ ገሥጸው።

18 “ ‘ወገንህን አትበቀል፤ ወይም በመካከልህ ከሚኖር በማንኛውም ሰው ላይ ቂም አትያዝ፤ ነገር ግን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

19 “ ‘ሥርዐቴን ጠብቁ። “ ‘የተለያዩ እንስሳትን አታዳቅል። “ ‘በዕርሻህ ላይ ሁለት ዐይነት ዘር አትዝራ። “ ‘ከሁለት ዐይነት ነገር የተሠራ ልብስ አትልበስ።

20 “ ‘አንድ ሰው ለሌላ ከታጨች ሴት ባሪያ ጋራ ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ ሴቲቱም ያልተዋጀች ወይም ነጻ ያልወጣች ብትሆን ይቀጣል፤ ነገር ግን ሴቲቱ ነጻ ስላልወጣች አይገደሉም።

21 ሰውየውም ለበደል መሥዋዕት የሚሆን አንድ አውራ በግ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ለእግዚአብሔር ያምጣ።

22 ካህኑም በበደል መሥዋዕቱ አውራ በግ፣ ሰውየው ስለ ሠራው ኀጢአት በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል፤ ኀጢአቱም ይቅር ይባልለታል።

23 “ ‘ወደ ምድሪቱ ገብታችሁ ማንኛውንም ዐይነት ፍሬ የሚሰጥ ዛፍ በምትተክሉበት ጊዜ፣ ፍሬው ለመብላት ያልተገረዘ መሆኑን ዕወቁ፤ ለሦስት ዓመትም የተከለከለ በመሆኑ አይበላ።

24 በአራተኛውም ዓመት ፍሬው ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ የምስጋና መሥዋዕት ይሆናል።

25 በዐምስተኛው ዓመት ግን ፍሬውን ትበላላችሁ፤ በዚህም ሁኔታ ፍሬው ይበዛላችኋል፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።

26 “ ‘ደም ያለበትን ማንኛውንም ሥጋ አትብሉ። “ ‘ጥንቈላ ወይም አስማት አትሥሩ።

27 “ ‘የራስ ጠጕራችሁን ዙሪያ አትከርከሙ፤ ጢማችሁንም አሳጥራችሁ አትቍረጡ።

28 “ ‘ለሞተ ሰው ሰውነታችሁን አትንጩ፤ በሰውነታችሁም ላይ ንቅሳት አታድርጉ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

29 “ ‘ምድሪቱ ወደ ግልሙትና አዘንብላ በርኩሰት እንዳትሞላ፣ ሴት ልጅህ ጋለሞታ ትሆን ዘንድ አታዋርዳት።

30 “ ‘ሰንበታቴን ጠብቁ፤ መቅደሴንም አክብሩ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

31 “ ‘እንዳትረክሱባቸው ወደ ሙታን ጠሪዎች ዘወር አትበሉ፤ መናፍስት ጠሪዎችንም አትፈልጉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።

32 “ ‘ዕድሜው ለገፋ ተነሥለት፤ ሽማግሌውን አክብር፤ አምላክህንም ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

33 “ ‘መጻተኛ በምድራችሁ ላይ ዐብሯችሁ በሚኖርበት ጊዜ አትበድሉት፤

34 ዐብሯችሁ የሚኖረው መጻተኛ እንደ ገዛ ወገናችሁ ይታይ፤ እንደ ራሳችሁም ውደዱት፤ እናንተም በግብጽ መጻተኞች ነበራችሁና፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።

35 “ ‘በመስፈሪያ ወይም በሚዛን አታጭበርብሩ።

36 የጽድቅ መለኪያ፣ የጽድቅ ሚዛን፣ የጽድቅ የኢፍ መስፈሪያ፣ የጽድቅ የሂን መስፈሪያም ይኑራችሁ። ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።

37 “ ‘ሥርዐቴንና ሕጌን ሁሉ ጠብቁ፤ ተከተሏቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች