ናሆም 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበነነዌ ላይ የተገለጠ የእግዚአብሔር ቊጣ 1 ስለ ነነዌ ጥፋት ኤልቆሻዊው ናሆም የተናገረው ቃልና ያየው ራእይ የሚከተለው ነው። 2 እግዚአብሔር ቀናተኛ ተበቃይ አምላክ ነው፤ በኀይለኛ ቊጣውም፥ በጠላቶቹ ላይ መዓቱን ያወርዳል። 3 እግዚአብሔር ታጋሽና ኀያል ነው፤ ነገር ግን በደለኛውን ሳይቀጣው አያልፍም፤ መንገዱ በዐውሎ ነፋስና በሞገድ ውስጥ ነው፤ ሰው ሲራመድ ትቢያን እንደሚያስነሣ፥ የእግዚአብሔርም መገለጥ ደመናን ያስከትላል። 4 እግዚአብሔር ባሕሩንና ወንዞቹን ገሥጾ ያደርቃቸዋል። በባሳንና በቀርሜሎስ የሚገኙ ዕፀዋት ይደርቃሉ፤ የሊባኖስም አበቦች ይጠወልጋሉ። 5 በእግዚአብሔር ፊት ተራራዎች ይንቀጠቀጣሉ፤ ኰረብቶችም ይቀልጣሉ፤ በእግዚአብሔር ፊት ምድር ትናወጣለች፤ ዓለምና በውስጥዋ የሚኖሩ ሁሉ ይንቀጠቀጣሉ። 6 በእርሱ ኀይለኛ ቊጣ ፊት መቆም የሚችል ማን ነው? ቊጣውስ እንደ እሳት በነደደ ጊዜ የሚችለው ማነው? እንደ እሳት የሚያቃጥል ቊጣው በሚወርድበት ጊዜ አለቶች ተሰነጣጥቀው ይበታተናሉ። 7 እግዚአብሔር ቸር ነው፤ በመከራ ጊዜም ጠንካራ መሸሸጊያ ነው፤ በእርሱ የሚተማመኑትን ሁሉ ይንከባከባል። 8 ተቃዋሚዎቹን በኀይለኛ ጐርፍ ያጥለቀልቃቸዋል፤ ጠላቶቹንም ወደ ጨለማ ያሳድዳቸዋል። 9 እናንተ በእግዚአብሔር ላይ የምታሤሩት ለምንድን ነው? እርሱ እናንተን እስከ መጨረሻው ይደመስሳችኋል፤ ዳግመኛም በእርሱ ላይ መነሣሣት ከቶ አትችሉም። 10 እናንተ ሰካራሞች! እርስ በርሱ የተያያዘ እሾኽና ድርቆሽ በእሳት ተቃጥሎ እንደሚጠፋ፥ እናንተም እንዲሁ ትጠፋላችሁ። 11 የነነዌ ሕዝብ ሆይ! በእግዚአብሔር ላይ ሤራ የሚያሤርና ክፉ ምክር የሚመክር ሰው ከመካከላችሁ ተነሥቶአል። 12 እግዚአብሔር ለሕዝቡ ለይሁዳ እንዲህ ይላል፦ “አሦራውያን ኀይለኞችና ቊጥራቸው የበዛ ቢሆንም እንኳ ተደምስሰው እንዳልነበሩ ይሆናሉ። ሕዝቤ ሆይ! ከዚህ በፊት መከራ ያጸናሁባችሁ ቢሆንም እንኳ ከእንግዲህ ወዲህ ይህን አላደርግባችሁም። 13 አሦራውያን በእናንተ ላይ የጫኑትን የጭቈና አገዛዝ አስወግዳለሁ፤ እናንተን ያሰሩበትንም እግር ብረት እሰብራለሁ።” 14 እግዚአብሔር ስለ አሦራውያን የሰጠው ፍርድ እንዲህ የሚል ነው፦ “ከእንግዲህ ወዲህ ስማችሁን የሚያስጠራ ተተኪ ዘር አይኖራችሁም፤ በአማልክታችሁ ቤተ መቅደስ የሚገኙትን የተቀረጹ ምስሎችንና ቀልጠው የተሠሩ ጣዖቶችን አጠፋለሁ፤ እናንተም ዋጋ ቢሶች ስለ ሆናችሁ የመቃብር ጒድጓድ እምስላችኋለሁ።” 15 እነሆ መልካም ዜናን የሚያበሥር፥ ሰላምንም የሚያውጅ መልእክተኛ በተራሮች ላይ እየመጣ ነው። የይሁዳ ሕዝብ ሆይ! ክፉዎች ጠላቶችህ ፈጽሞ ስለ ተደመሰሱ ከእንግዲህ ወዲህ አገርህን ከቶ አይወሩአትም! ስለዚህ ዓመት በዓሎችህን በደስታ አክብር! ስእለትህንም ለእግዚአብሔር ስጥ! |