የኢዮአብም መልእክተኛ ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ንጉሡ ሄደ። ደርሶም ኢዮአብ የነገረውን የጦርነቱን ዜና ሁሉ ለዳዊት ነገረው። ዳዊትም በኢዮአብ ላይ ተቈጣ። ያንም መልእክተኛ፥ “ትዋጉ ዘንድ ወደ ከተማዋ ቅጥር ለምን ቀረባችሁ? በቅጥሩም እንደምትቈስሉ አታውቁምን? የይሩበዓል ልጅ አቤሜሌክን ማን ገደለው? አንዲት ሴት ከቅጥር ላይ የወፍጮ መጅ ጥላበት በቴቤስ የሞተ አይደለምን? ስለምን ወደ ቅጥሩ ቀረባችሁ?” አለው።