1 ይፈትኑት ዘንድ ነው እንጂ፥ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰውን መከራ አያገኘውም፤ ከመከራዪቱም ይድናል። 2 ብልህ ሰው መጽሐፍ መስማትን ይወድዳል፤ የሚጠራጠርና በመጽሐፉ የማያምን ሰው ግን በጥቅል ነፋስ መካከል እንደምትንጓለል መርከብ ይሆናል። 3 ብልህ ሰው አምኖ በእግዚአብሔር ሕግ ይገዛል፤ እግዚአብሔርም የታመነ ወዳጁ ይሆናል፤ ደስም ያሰኘዋል። 4 የምትናገረውን ነገርህን አዘጋጅተህ አድምጥ፤ የምታደርገውንም ምክር አጽንተህ ተናገር። 5 የሰነፍ ሰው ልቡና እንደ ሰረገላ መንኰራኵር ነው፤ የፈሪ ሰው ምክርም እንደምትሽከረከር እንዝርት ነው። 6 ጮሌ ፈረስ እንደ በጎ ወዳጅ ነው። በሚጋልበውም ሁሉ በታች ያሽካካል። 7 የዓመቱ ቀን ሁሉ በፀሐይ ብርሃን ጸንቶ ሲኖር፥ አንዲቱ ቀን ካንዲቱ ቀን በምን ትበልጣለች? 8 ቀኑ ሁሉ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ይለያል፤ የበዓላቱም ጊዜ በቍጥሩ ይታወቃል። 9 ከቀኑም የቀደሰውና ያከበረው አለ። ከእነርሱም በየጊዜያቸውና በየቍጥራቸው ክረምትንና መጸውን፥ በጋንም ለየ። 10 እኛ ሁላችን የአዳም ልጆች ከመሬት ተገኘን፤ አዳምም ከመሬት ተፈጠረ። 11 እግዚአብሔርም በጥበቡ ብዛት ለያቸው፤ በየመንገዳቸውም አዘጋጃቸው። 12 ከእነርሱም የባረካቸውና ከፍ ከፍ ያደረጋቸው አሉ፤ ከእነርሱም የቀደሳቸውና የተገለጠላቸው አሉ። ከእነርሱም የረገማቸውና ያጐሳቈላቸው አሉ፤ እንደ ሥራቸውም የወነጀላቸው አሉ። 13 እኛ ሁላችን በእርሱ ዘንድ በሸክላ ሠሪ እጅ እንዳለ ጭቃ፥ ነን፤ ፍጥረቱ ሁሉ በመንገዶቹ ይሄዳል፤ ሰውም እንዲሁ በፈጣሪው እጅ ነው፤ ለሁሉም እንደ ሥራው ይከፍለዋል። 14 የክፋት ተቃራኒዋ በጎነት ናት፤ የሞትም ተቃራኒዋ ሕይወት ናት፤ እንደዚሁ የጻድቅ ተቃራኒው ኃጥእ ነው። 15 ከዚህ ሁሉ ጋር የልዑልን ፍጥረቶች ተመልከት፤ አንዱ የሌላው ተቃራኒ ሆኖ ሁለት ሁለት ናቸው። 16 እኔ ግን ከሁሉ በኋላ ተነሥቼ ይኽን ነገር አሰብሁት፥ ከጥንቱም ጀምሬ መረመርሁት። 17 አቤቱ በስምህ የተጠሩ ወገኖችህን ይቅር በል፤ የበኵር ልጄ ያልሃቸው እስራኤልንም ይቅር በል። 18 ቅድስት ከተማህን፥ ማረፊያ ቦታህን ኢየሩሳሌምንም ይቅር በል። 19 ጽዮንንም የቃልህን በረከት ሙላት፤ ክብርህንም በወገኖችህ ላይ ሙላ። 20 አስቀድሞ ለፈጠርሃቸው ሕግህን ስጣቸው፤ ለስምህም ነቢያትን አስነሣ። 21 ነቢያትህን ያምኗቸው ዘንድ ተስፋ ላደረጉህ ዋጋቸውን ስጣቸው። አቤቱ የባሮችህ የነቢያትን ጸሎታቸውን ስማ፤ 22 የአሮንንም በረከት በሕዝብህ ላይ አሳድር፤ በምድር የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ዘለዓለማዊ አምላክ እግዚአብሔር አንተ ብቻ እንደ ሆንህ ይወቁ። 23 እህል ሁሉ ይበላል፤ ወደ ሆድም ይወርዳል፤ ነገር ግን ከእህል የሚጣፍጥ እህል አለ። 24 የእህልን ጣዕም ሁሉ ጕሮሮ ይለየዋል፥ እንደዚሁም ሁሉ የጠቢብ ሰው ልብ የሐሰት ነገርን ይለያል። 25 ክፉ ልቡና ኀዘንን ያመጣል፤ ብዙ መከራ የተቀበለ ሰውም ትዕግሥትን ይለምደዋል። 26 ወንድ ሁሉ ሚስት ያገባል፤ ነገር ግን ከሴት የምትሻል ሴት አለች። 27 የሴት ውበቷ ፊትን ያበራዋል፤ ከሰው ፈቃድ ሁሉ እርሷ ትበልጣለች። 28 የዋህ ብትሆን፥ ቃሏም ያማረ ቢሆን፤ ባሏ እንደ ሌሎች ሰዎች አይደለም። 29 ረዳቱ፥ መደገፊያ ምሰሶውም ናትና፥ ልባም ሴትን ያገባ ሰው ደስታውን አገኘ። 30 ቅጥር የሌለው ቤት ገንዘቡ እንዲሠረቅ፥ እንደዚሁም ሚስት የሌለችው ሰው ተቸግሮ ይኖራል። 31 ከከተማ ወደ ከተማ የሚዞር ሌባን የሚዋሰው ማን ነው? ልጆች የሌሉት፥ ንብረትም የሌለውና በመሸበት የሚያድር ሰውም እንዲሁ ነው። |