ስለ ሕልም ከንቱነት1 ሰነፍ ሰው ግን ሐሰትን በከንቱ ተስፋ ያደርጋታል፤ ሕልምም ሰነፍ ሰውን ያስደነግጠዋል። 2 ሕልምን የሚያምን ሰው ጥላን እንደሚጨብጥ፤ ነፋስንም እንደሚከተል ነው። 3 ሕልም ከዚህ ወደዚህ ይሄዳል፤ በየምሳሌውም የእየራሱን ያሳያል። 4 ከርኩስ ምን ንጹሕ ይወጣል? ከሐሰትስ እውነት ከየት ይገኛል? 5 ሕልም፥ ጥንቆላና ሟርት ሁሉም ከንቱ ናቸው፤ ልብንም ያስደነግጣሉ፤ እንደ ምጥም ያጎብጣሉ። 6 ይቅር ይል ዘንድ ከእግዚአብሔር የተላከ ከአልሆነ፥ በልብህ አታኑረው። 7 ሕልም ብዙ ሰዎችን አስትዋቸዋልና፤ እርሱንም ተስፋ እያደረጉ ጠፍተዋልና። 8 ያለ ሐሰትስ ከታየ በእውነት ይደርሳል፤ የእውነት ቃልም የተረዳ ይሆናል። 9 የተማረ ሰው ብዙ ምክርን ያውቃል፤ ብዙ መከራን የተቀበለ ሰውም ጥበብን ያስተምራል። 10 ያልተነካ ሰው ግን የሚያውቀው ነገር የለም። 11 ብዙ መከራ የተቀበለ ሰው ብዙ ትምህርት ይማራል። 12 መከራን በተቀበልሁ ጊዜ ብዙ አየሁ፤ ከአሳቤም ቃሌ በዛ። 13 ለሞት እስክደርስ ድረስ ሁልጊዜ መከራን ተቀብያለሁና፤ ስለዚህም ነገር እግዚአብሔር ያድነኛል። 14 እግዚአብሔርን የምትፈራ ነፍስ ትድናለች። 15 እርሱን ተስፋ ያደረጉ ሁሉ ይድናሉ። 16 እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰውን የሚያስፈራው የለም፤ እርሱ አለኝታው ነውና አይደነግጥም። 17 እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ነፍስ ብፅዕት ናት። 18 እርሱ ያድርበታልና፥ የታመነ ወዳጁም ነውና። 19 የእግዚአብሔር ዐይኖቹ ወደ ወዳጆቹ ናቸው፤ ኀይሉ የታመነ ነው፤ ጥግነቱም ጽኑ ነው፤ ቃጠሎውን ያቀዘቅዝልሃል፤ ከቀትር ፀሐይም ይጋርድሃል፤ ከዕንቅፋት ይጠብቅሃል፤ ከመውደቅም ይረዳሃል። 20 ሰውነትህን ያገናታል፤ ዓይኖችህንም ያበራቸዋል፤ ይፈውሳል፤ ደኅንነትንም ይሰጣል፤ በረከትንም ያጠግባል። 21 የበደል መባእ መሥዋዕት ርኩስ ነው፤ የኀጢአተኞችም ቍርባናቸው የረከሰ ነው። 22 የኀጢአተኞችም መባእ ተቀባይነት የለውም። 23 በመባህ ብዛት ኀጢአትህ የሚሰረይልህ አይደለም። 24 በዐመፃ ገንዘብ መባእን የሚያገባ ሰው፤ ሕፃንን በአባቱ ፊት እንደሚገድል ሰው ነው። 25 የድሃ ሕይወቱ ምጽዋት መለመን ነው፤ እምቢ ያለው ሰው ግን ነፍሰ ገዳይ ነው። 26 ባልን ከሚስቱ የሚያፋታ ሰው፥ ባልንጀራውን እንደሚገድል ሰው ነው። 27 የምንደኛውን ደመወዝ የቀማ ሰው፥ ደሙን ማፍሰሱ ነው። 28 አንዱ ሲሠራ አንዱ ቢያፈርስ፥ የሁለቱስ ድካማቸው ምን ይጠቅማል? 29 አንዱ ሲመርቅ ሌላው ቢረግም፥ ከሁለቱ የማናቸውን ቃል ይሰማል? 30 ሬሳ ከዳሰሰ በኋላ እጁን ቢታጠብ፥ ዳግመኛ ሬሳውን ከዳሰሰ መታጠቡ ምን ይጠቅመዋል? 31 እንዲሁ ስለ ኀጢአቱ የሚጾም ሰው ዳግመኛ ይበድል ዘንድ ከሄደ፥ ከዚህ በኋላ ጸሎቱን ማን ይሰማዋል? ሰውነቱንስ ማሳዘኑ ምን ይጠቅመዋል? |