ስለ እስራኤል ደኀንነትና መታደስ የቀረበ ጸሎት1 የዓለም ጌታ አምላክ ሆይ፥ ወደ እኛ ተመልከት፥ ራራልን፤ ሌሎች ሕዝቦችም ይፈሩህ ዘንድ አድርግ። 2 በአገሮች ላይ ሁሉ እጅህን አንሣ፤ ኃያልነትህንም አሳያቸው። 3 በእነርሱ ፊት ለእኛ ቅድስነትህን እንዳሳየኸን ሁሉ፥ አሁን ደግሞ በእኛ ፊት ታላቅነትህን ለእነርሱ አሳያቸው። 4 እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ! ካንተ በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ እኛ እንዳወቅን፥ እነርሱም ያውቁህ ዘንድ አድርግ። 5 አዳዲስ ምልክቶችን ላክ፤ ታምራቶችንም ሥራ፤ ለእጅህና ለቀኝ ክንድህ ክብርን ስጥ። 6 ቁጣህን አምጣ፤ መዓትህን አውርድ፤ ተቃዋሚህን አጥፋ፤ ጠላትህንም ደምስስ። 7 ቀኑን አፍጥን፤ የገባኸውን ቃል አስታውስ፤ ስለ አስደንጋጭ ሥራህም ይነገር። 8 ቀሪዎቹን ሰዎች ነበልባላዊ ቁጣህ ይብላቸው፤ ሕዝብህን የጨቆኑ ይደምሰሱ። 9 የጨካኝ መሪዎችን፥ ከእኛ ሌላ ማንም የለም! የሚሉትን ሁሉ፥ ጭንቅላታቸውን አፍርስ። 10 የያዕቆብን ነገዶች አሰባስብ፤ እንደ መጀመሪያው ጊዜም ርስታቸውን መልሰህ ስጣቸው። 11 ጌታ ሆይ! በስምህ ለሚጠራው የክብር ልጅህ ለሆነው ለእስራኤል ራራለት። 12 ለቅድስት ከተማህ፥ ማረፊያህ ለሆነችው ለኢየሩሳሌም ርኀራኄ ይኑርህ። 13 ጽዮንን በምስጋናህ፥ ቤተ መቅደስህን በክብርህ ሙላት። 14 በመጀመሪያ የፈጠርኻቸውን አንጻቸው፤ በስምህ የተተነበየውን ሁሉ ፈጽም። 15 አንተን ለሚጠብቁህ ሁሉ ሽልማታቸውን ስጥ፤ ነቢዮችህም ትክክለኞች እንደ ነበሩ አረጋግጥ። 16 ጌታ ሆይ! የአሮንን ምርቃት እንደተቀበልህ፥ የአገልጋዮችህንም ጸሎት እንዲሁ ተቀበል። 17 በዓለም ላይ የሚኖሩ ሰዎችም ሁሉ፥ ጌትነትህንና ዘላለማዊ አምላክነትህን ይቀበላሉ። መለየት18 ሆዳችን ሁሉንም ዓይነት መብል ይቀበላል፤ አንዳንዶቹ ግን ከሌሎቹ የተሻሉ ናቸው። 19 ምላስ የሥጋን ጣዕም እንደሚለይ ሁሉ፥ አስተዋል አድማጭም የውሸት ቃልን ይለያል። 20 ተንኮለኛ ሰው ሌሎችን ያሳዝናል፤ እንዲህ ዓይነቱን ለመቀበል ልምድ ያሻል። ሚስት መምረጥ21 ሴት የመጣላትን ባል ትቀበላለች፤ አንዳንድ ሴት ልጆች ግን ከሌሎች የተሻሉ ናቸው። 22 የሴት ልጅ ውበት ተመልካቹን ያስደስታል፤ ወንድ ከዚህ የተሻለ የሚወደው ነገር የለም። 23 ምላሷ ደግና ልስልስ ከሆነ፥ ባሏ ከወንዶች ሁሉ ደስተኛ ነው። 24 ሚስት የሚያገባ ሰው ወደ መልካም ዕድል መንገዱን አቅንቷል፤ እርሱን የምትመስል ረዳትና ደጋፊ ምሰሶም አፍርቷል። 25 ንብረት ያለ አጥር የዘራፊ ሲሳይ ነው፤ ሚስት የሌለውም ወንድ እንዲሁ ዓላማ ቢስና ብስጩ ይሆናል። 26 ከተማ ለከተማ የሚራወጠውንና የታጠቀውን ሌባ የሚያምን ይኖራልን? 27 ጐጆ የሌለውና በመሸበት የሚያድርም ሰው እንዲሁ ነው። |