የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ

ማስታወቂያዎች

መላው መጽሐፍ ቅዱስ ብሉይ ኪዳን አዲስ ኪዳን


መጽሐፈ ሲራክ 31 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)
መጽሐፈ ሲራክ 31

ሀብት

1 ሀብት የሚያመጣው የእንቅልፍ እጦት፤ ሰውነት ያከሳል፤ የሚያስከትለው ጭንቀትም እንቅልፍ ያባርራል።

2 የቀኑ ጭንቀት አያስተኛም፤ እንደ ክፉ ደዌም እንቅልፍ ያሳጣል።

3 ሀብትም ሁልጊዜ ይደክማል፤ ገንዘብ ያከማቻል፤ ሲያርፍም በምቾት ይንደላቀቃል።

4 ድሀ ሁልጊዜ ይደክማል፤ ኑሮውም ከእጅ ወደ አፍ ነው፤ ሲያርፍም ይበልጥ ይደኸያል።

5 ገንዘብ የሚወድ ከቶውንም ከኃጢአት አይነጻም፤ ትርፍ አሳዳጅም ከጥፋት ይወድቃል።

6 ወርቅ ብዙዎችን አስቷል፤ ራሳቸውን ለጥፋት የዳረጉትም እነርሱ ናቸው።

7 ለእርሱ መሥዋዕት የሚያቀርቡና አላዋቂዎች ሁሉ፥ በእርሱ ወጥመድ ይገባሉ።

8 ወቀሳ የማይገኝበት፥ ለወርቅ ያላደረ ሀብታም የታደለ ነው።

9 ከወገኖቹ መካከል እንዲህ የተደነቀው ማነው? እንኳን ደስ ያለህ ልንለው እንሻለን።

10 ይህን ፈተና በአሸናፊነት የተወጣ ይኖራልን? ካለ ግን በእርግጥም ሊኮራ ይገባዋል! በኃጢአት መውደቅ ሲገባው ያልወደቀ፥ ማጥፋት ሲኖርበት ያላጠፋ ይገኛልን?

11 ሀብቱ በጽኑ መሠረት ላይ ይገነባል፤ ጉባዔውም ደግነቱን ይመሰክርለታል።

የራት ግብዣዎች

12 ከሚያስጐመዥ ማዕድ ፊት ስትቀርብ ስግብግብነትን አታሳይ፤ የሚበላው ተትረፍርፏልም አትበል።

13 የዐይን ስስት የሚያስቀይም መሆኑን አትዘንጋ፤ በፍጥረት ውስጥ እንደ ዐይን የከፋ ነገር አለን? ሁሌም እንባ የሚያነባው ለዚህ ነው።

14 የአስተናጋጅህ ዐይን ያረፈበትን ነገር አትንካ፤ ለማዕድ ስትቀርቡም አትጋፋው።

15 የባልንጀራህን ፍላጐት እንደ ራስህ ፍረድ፤ በሁሉም መልክ አሳቢ ሁን።

16 በሥርዓት እንዳደገ ሰው የቀረበልህን ተመገብ፤ ምግቡን አትጐስጐስ፤ መጠላት ታተርፋለህና።

17 ትሕትህናን ቀድመህ መብላት በማቆም አስመስክር፤ ሰዎችን እንዳታስቀይም አጋቦስ አትሁን።

18 ከብዙ ሰዎች ጋር ከተቀመጥህ ከሌሎቹ ቀድመህ እጅህን አትዘርጋ።

19 መልካም አስተዳደግ ላለው የሚበቃው ትንሽ ነው፤ ሲተኛም በቀላሉ ይተነፍሳል።

20 የተመጠነ ምግብ ጥሩ እንቅልፍ ይሰጣል፤ ንቁና ደስተኛም ያደርጋል፤ የአጋቦስ ትርፉ እንቅልፍ ማጣት፥ የሆድ ሕመምና የምግብ አለመፈጨት ነው።

21 ብዙ ለመብላት ከተገደድህ ተነስ! ወጥተህም አስመልስ! ፈጥኖም ይሻልሃል።

22 ልጄ ሆይ አትናቀኝ፥ እኔን አድምጠኝ፤ የቃሌንም ምንነት እያደር ትረዳለህ፤ በምታደርገው ሁሉ እርጋታ ይኑርህ፤ ሕመምም ጨርሶ አይነካህም።

23 የተዋጣለት ግብዣ የሚያደርገውን ሰው፥ ሰዎች ያመሰግኑታል፤ ቸርነቱንም ያደንቃሉ።

24 ንፉግ አስተናጋጅ ቅሬታን ያተርፋል፤ ሕዝቡም ክፋቱን ያወሩበታል።

ወይን ጠጅ

25 ብዙ ሰዎችን ስላጠፋ ወይን ጠጅን አትድፈር።

26 እሳት የብረት ጥንካሬ መፈተኛ እንደ ሆነው ሁሉ፥ የጉረኞችም ልበ-ደንዳናት መለኪያው የወይን ጠጅ ነው።

27 በመጠኑ ከተጠጣ የወይን ጠጅ ሕይወት ነው። ሕይወት ያለ ወይን ጠጅ ትርጉሙ ምንድነው? የተፈጠረውም ሰዎችን ለማስደሰት ነው።

28 በተገቢው ወቅትና በአስፈላጊው መጠን ከተጠጣ፥ የወይን ጠጅ የልብ ተድላና የነፍስ ደስታ ነው።

29 የወይን ጠጅን በአጉል ድፍረት ከመጠን በላይ መጠጣት የነፍስ ምሬትን ያስከትላል።

30 ስካር አላዋቂውን ያስቆጣል፤ ኃይሉን ይቀንስዋል፤ አምባጓሮም ውስጥ ይጨምረዋል።

31 በወይን ጠጅ ግብዣ ላይ ጓደኛህን አትተንኩሰው፤ ደስ ባለው ሰዓት አትሳቅበት፤ በዚያን ሰዓት አትገሥጸው፤ ዕዳውንም ክፈል ብለህ አታበሳጨው።