የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ

ማስታወቂያዎች

መላው መጽሐፍ ቅዱስ ብሉይ ኪዳን አዲስ ኪዳን


መጽሐፈ ሲራክ 13 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)
መጽሐፈ ሲራክ 13

ከእኩዮችህ ጋር ዋል

1 ቅጥራን የሚነካ ያድፋል፤ ከትዕቢተኛም ጋር የሚውል እርሱን ይመስላል።

2 ከአቅምህ በላይ የሆነን ሸክም ለማንሳት አትሞክር፤ ከአንተ የበለጠ ኃያልና ሃብታም ከሆነው ጋር አትጎዳኝ፤ ስለምን የሸክላውን ማሰሮ ከብረት ድስት ጎን ታኖራልህ? ሁለቱ ሲጋጩ ይሰበራልና።

3 ሀብታም በድሎ ይቆጣል፤ ድኃ ተበድሎ ይቅርታ ይለምናል።

4 ከጠቀምከው ይገለገልብሃል፤ ካጣህ ይተውሃል።

5 ገንዘብ አለህን? ካለህ ከአንተ ጋር ይኖራል፤ ያለምንም አስተያየት ባዶ ያስቀርሃል።

6 ታስፈልገዋለህ? ከሆነ ያታልልሃል፥ ይስቅልሃል፥ ተስፋም ይሰጥሃል፥ በትሕትና ያናግርሃል፥ ምን ላድርግልህ? ብሎ ይጠይቅሃል።

7 በራት ግብዣው ላይ ያዋርድሃል፥ ሁለቱ ወይም ሦስቱ ያለህን ካሟጠጠ በኋላ ይስቅብሃል፤ ከዚህ በኋላ ባየህ ቍጥር ፊቱን ይመልስብሃል፥ ራሱን ይነቀንቅብሃል።

8 እንዳትታለል ተጠንቀቅ፤ በሞኝነትህ እንዳትዋረድ እራስህን ጠብቅ።

9 ሹም ሲጋብዝህ ቸልተኛ ምሰል፤ እርሱም ግብዣውን ደጋግሞ ያቀርብለሃል።

10 እንዳይገፋህ አትጣደፍ፤ እንዳይረሳህ አትራቅ፤

11 እንደ አቻህ አትቅረበው፤ የቃላቱንም አወራረድ አትመን፤ ምክንያቱም ንግግሩ አንተን መፈተኛ ነው፤ በወዳጅነት ሽፋንም ይመዝንሃል።

12 ወሬ ቸርቻሪ ምሕረት የለውም፤ አንተን ከመደብደብና ከማሰር አይቆጠብም።

13 ተጠበቅ፥ በጣም ተጠንቀቅ፤ የምትጓዘው ከውድቀትህ ጋር ነውና።

15 ሕይወት ያለው ፍጥረት ሁሉ መሰሉን፥ ሰው ሁሉ ባልንጀራውን ይወዳል።

16 ሁሉም ፍጡር ከመሰሉ ጋር ይቀላቀላል፤ ሰዎችም ከመሰሎቻቸው ጋር ይቀራረባሉ።

17 ተኩላና በግ ምን አንድነት አላቸው? ኃጢአተኛም በጻድቅ ፊት እንዲሁ ነው።

18 በጅብና በውሻ መሀል ምን ሰላም ይገኛል? በሀብታምና በድኃ መሐልስ እንዲሁ አይደለምን?

19 የሜዳ አህዮች በበረሃ የአንበሶች ግዳይ ናቸው፤ ድሆችም እንዲሁ የሀብታሞች ሰለባ ናቸው።

20 ትዕቢተኞች ትሕትናን እንደሚጠሉት ሁሉ፥ ሀብታሞችም ድሆችን እንዲሁ ይጠላሉ።

21 ሀብታም ሲወድቅ ወዳጆቹ ይደግፉታል፤ ድኃ ሲወድቅ ወዳጆቹ ይገፉታል።

22 ሀብታም ሲያዳልጠው የሚይዙት እጆች በርካታ ናቸው። ንግግሩ ፍሬቢስ እንኳ ቢሆን ያደንቁለታል፤ ድኃው ሲያዳልጠው ይነቀፋል፤ መልካም ነገር ቢናገም ቦታ የሚሰጠው የለም።

23 ሀብታም ሲናገር ሁሉም ያዳምጣል፤ ንግግሩንም ከፍ ከፍ ያደርጉለታል። ድኃ ሲናገር ይህ ማነው ይባላል፤ ቢደናቀፍም ገፍተው ይጥሉታል።

24 በደለኞች “ኃጢአት በሌለበት ሀብት ጥሩ ነው፤ ድህነት ግን መጥፎ ነው” ይላሉ።

25 በደግም ሆነ በክፉ የሰውን ገጽታ የሚቀይረው ልቦናው ነው።

26 ፈገግታ የሞላበት ገጽታ የደስተኛ ልብ ምልክት ነው። ምሳሌዎችን መፍጠር ግን አድካሚ ሥራ ነው።