የቤቱሊያ መያዝ በእስራኤል ላይ የተደረገ ዘመቻ1 በማግሥቱ ሆሎፎርኒስ ወታደሮቹን ሁሉና ሊያግዙት የመጡትን ሰዎች ሁሉ ሠፈራቸውን ለቀው ወደ ቤቱሊያ ጉዞ እንዲጀምሩና የተራራማውን አገር መተላለፊያዎች እንዲይዙ፥ ከእስራኤል ልጆች ጋር ጦርነት እንዲገጥሙ አዘዘ። 2 በዚያን ቀን ኃያላን ሰዎቻቸው በሙሉ ከጦር ሰፈራቸው ወጡ፥ ተዋጊዎቹ ቁጥራቸው መቶ ሰባ ሺህ እግረኛና ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሰኛ ጦር ነበረ ይህም ጓዝ የሚጠብቁና እጅግ ብዙ እግረኛ ሰዎች ሳይቆጠሩ ነው። 3 ከቤቱሊያ አጠገብ ባለው ሸለቆ ከምንጩ ዳር ሰፈሩ፤ በስፋት ከዶታን እስከ ቤልባይም በርዝመት ደግሞ ከቤቱሊያ በኤስድራሎን ፊት ለፊት እስከሚገኘው እስከ ሳያሞን ድረስ ተስፋፉ። 4 የእስራኤል ልጆች ብዛታቸውን በአዩ ጊዜ እጅግ ደነገጡ፥ እርስ በርሳቸውም፦ “አሁን ምድርን ሁሉ ይጨርሱአታል፥ ታላላቅ ተራሮችም ቢሆኑ፥ ሸለቆዎችም ቢሆኑ፥ ኮረብቶች ቢሆኑ ሸክማቸውን መሸከም አይችሉም” ተባባሉ። 5 ሁሉም የጦር መሣሪያቸውን ያዙ፥ በግንቦቻቸው ላይ እሳት አንድደው ሌሊቱን ሙሉ ሲጠብቁ አደሩ። 6 በሁለተኛው ቀን ሆሎፎርኒስ በቤቱሊያ በሚገኙ እስራኤላውያን ፊት ፈረሰኞቹን ሁሉ አወጣ። 7 የከተማቸውን መግቢያ በሚገባ ሰለለ፤ የውሃ ምንጫቸውን አየና እንዲያዝ አደረገ፥ እንዲጠብቁትም ወታደሮችን አቆመ፥ እርሱ ወደ ሕዝቡ ተመለሰ። 8 የኤሳው ልጆች ገዢዎች ሁሉና የሞዓብ ሕዝብ አለቆች ሁሉ እንዲሁም የባሕር ጠረፍ አዛዦች ወደ እርሱ መጡ፥ እንዲህም አሉ፦ 9 ጌታ ሆይ በሠራዊትህ ላይ እልቂት እንዳይመጣ የምንነግርህን ስማ፤ 10 ይህ ሕዝብ፥ እነዚህ የእስራኤል ልጆች በጦራቸው አይተማመኑም ነገር ግን የሚተማመኑት በሚኖሩባቸው ተራሮች ነው፤ ወደ ተራሮቻቸው ጫፍ መውጣት አይቻልምና። 11 ስለዚህ ጌታ ሆይ በሰልፍ ሥርዓት አትዋጋቸው፥ ከአንተ ወገን አንድ ሰው እንኳ አይወድቅም፤ 12 አንተ የጦር ሠራዊትህን ይዘህ እዚሁ ሰፈር ቆይ፥ አገልጋዮችህ ከተራራው ሥር የሚመነጨውን የውሃ ምንጭ ይቆጣጠሩ፤ 13 ምክንያቱም የቤቱሊያ ነዋሪዎች ውኃ የሚቀዱት ከዚህ ነው፤ ውኃ ጥም ይገድላቸዋል፥ ስለዚህ ከተማቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ፤ በዚያን ጊዜ እኛና ሕዝቡ ወደ ተራራው ጫፍ አጠገብ እንወጣና ከከተማው ማንም ሰው እንዳይወጣ እንጠብቃለን። 14 እነርሱ፥ ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸውም በረኃብ ያልቃሉ፥ ሰይፍ ሳይመጣባቸው በሚኖሩባቸው ጎዳናዎች ይወድቃሉ። 15 አምጸዋልና በሰላምም አልተቀበሉህምና፥ ክፋትን መልሰህ ትከፍላቸዋልህ። 16 ቃላቸው ሆሎፎርኒስንና ሹማምንቱን ደስ አሰኘ፤ እነርሱ እንዳሉት እንዲደረግ አዘዘ፤ 17 ስለዚህ የአሞን ልጆች ሠራዊትና ከእነርሱም ጋር አምስት ሺህ አሦራውያንም ሄዱ፥ ሸለቆውንም ሰፈሩ፥ የእራኤላውያንን ውኃቸውንና ምንጮችን ያዙ። 18 የኤሳው ልጆችና የአሞን ልጆች ወጥተው በዶታይም ትይዩ ባለው ተራራማ አገር ሰፈሩ፤ ከእነሱም አንዳንዶቹን በሞኹር ወንዝ አጠገብ በኩሲ አቅራቢያ ወዳለው ወደ ደቡብና ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ ወደ ኤግሬቤ ላኩ፤ የቀሩት የአሦር ወታደሮች ሜዳ ላይ ሰፈሩ፥ ምድርን በሙሉ ሸፈኗት፤ ድንኳኖቻቸውና ጓዛቸው እጅግ ሰፊ ቦታ ያዘ፥ እጅግም ብዙ ሆኑ። 19 የእስራኤል ልጆች ወደ ጌታ አምላካቸው ጮኹ፤ መንፈሳቸው ዝላለችና፥ ጠላቶቻቸው ሁሉ ስለ ከበቧቸው፥ ከመካከላቸው ማምለጫ የለምና። 20 የአሦር ሠራዊት በሙሉ፥ እግረኞቻቸው፥ ሠረገላዎቻቸውና ፈረሰኞቻቸው ለሠላሳ አራት ቀን ከበቡአቸው፥ የቤቱሊያ ነዋሪዎች በዕቃቸው ያለ ውኃቸው ሁሉ አለቀ፤ 21 የውኃ ጉድጓዶችም ደረቁ፥ የሚጠጡት ውኃ ተመጥኖ ይሰጣቸው ስለ ነበር ለአንድ ቀን የሚጠጡት እንኳ አልነበራቸውም። 22 ሕፃናቶቻቸው ዛሉ፥ ሴቶችና ወጣቶች በውኃ ጥም አለቁ፥ በከተማይቱ አደባባዮችና በሮቹ ይወድቁ ነበር፥ ምንም ኃይል አልነበራቸውም። 23 ሕዝቡ ሁሉ ወጣቶች፥ ሴቶችና ሕፃናት በዑዚያና በከተማይቱ አለቆች አጠገብ ተሰበሰቡ፥ በሽማግሌዎች ሁሉ ፊት በኃይል እንዲህ እያሉ ጮሁ፤ 24 “በእኛና በእናንተ መካከል እግዚአብሔር ይፍረድ፤ ከአሦር ልጆች ጋር ሰላም ባለማድረጋችሁ ትልቅ ጉዳት አደረሳችሁብን፤ 25 ስለዚህ አሁን የሚረዳን ማንም የለም፤ እግዚአብሔር በውኃ ጥምና በታልቅ ጥፋት በፊታቸው እንድናልቅ በእጃቸው ጥሎናል፤ 26 አሁንም ጥሩአቸውና ከተማይቱን በሙሉ እንዲበዘብዙ ለሆሎፎርኒስ ሕዝብና ለሠራዊቱ ሁሉ አሳልፋችሁ ስጧቸው። 27 የእነርሱ ምርኮኞች መሆን ይሻለናል፥ ባሮቻቸው መሆናችን አይቀርም፥ ሆኖም በሕይወት እንኖራልን፤ ሕፃናቶቻችን በፊታችን ሲሞቱ፥ ሚስቶቻችንና ወጣቶቻችን የመጨረሻዋን ትንፋሽ ሲተነፍሱ አናይም። 28 ሰማይንና ምድርን እንዲሁም የአባቶቻችን ጌታ፥ በኃጢአቶቻችንና በአባቶቻኝ ኃጢአት እየቀጣን ያለውን እግዚአብሔርን እናስመሰክርባችኋለን፤ ዛሬ በዚች ቀን ይህን ነገር እንዳታደርጉ።” 29 በጉባኤው መካከል ጽኑ ልቅሶ ሆነ፤ በአንድ ድምፅ ወደ ጌታ እግዚአብሔር ጮኹ። 30 ዑዚያም እንዲህ አላቸው “ወንድሞቼ ሆይ አይዟችሁ! አምስት ቀን እንታገስ፤ ጌታ እግዚአብሔር ምሕረቱን ወደ እኛ ይመልሳል፥ እስከ መጨረሻው አይተወንምና። 31 ነገር ግን እነዚህ ቀኖች ካለፉ በኋላ እርዳታ ካልመጣልን እናንተ ተናገራችሁት አደርጋለሁ።” 32 ሕዝቡንም ወደየሰፈራቸው በተናቸው፤ እነርሱም ወደ ከተማቸው ምሽጐችና ግንቦች ሄዱ፤ ሴቶቹንና ልጆቹን ወደየቤታቸው ሰደዱአቸው፤ በከተማው ውስጥ ታላቅ መከራ ነበር። |