የሳኦል በዳዊት መቅናት1 ዳዊት ከሳኦል ጋር የሚያደርገውን ንግግር እንዳበቃ፤ የዮናታን ነፍስ ከዳዊት ነፍስ ጋር ተቆራኘች፤ እንደራሱም አድርጎ ወደደው። 2 ከዚያች ዕለት አንሥቶ ሳኦል ዳዊትን አብሮት እንዲኖር አደረገ፤ ወደ አባቱም ቤት እንዲመለስ አላሰናበተውም። 3 ዮናታን እንደ ራሱ አድርጎ ስለ ወደደው ከዳዊት ጋር ኪዳን አደረገ፤ 4 ዮናታን የለበሰውን ካባ አውልቆ ከነጦር ልብሱ፥ በተጨማሪም ሰይፉን፥ ቀስቱንና መታጠቂያውን ሰጠው። 5 ሳኦል በሚልከው በማናቸውም ስፍራ፥ ዳዊት ተልእኮውን በሚገባ ይፈጽም ስለ ነበር፥ በሠራዊቱ ላይ ሾመው፤ ይህም ሕዝቡን በሙሉ፥ የሳኦልንም የጦር ሹማምንት ደስ አሰኘ። 6 ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ከገደለ በኋላ፥ ሰዎቹ ወደየቤታቸው በሚመለሱበት ጊዜ፥ ሴቶች ከበሮና መሰንቆ ይዘው እየዘፈኑ፥ እየጨፈሩና እልል እያሉ ንጉሥ ሳኦልን ለመቀበል ከእስራኤል ከተሞች ሁሉ ወጡ። 7 ሴቶችም “ሳኦል ሺ ገዳይ! ዳዊት ዐሥር ሺ ገዳይ!” እያሉ በቅብብል ይዘፍኑ ነበር። 8 ሳኦል እጅግ ተቆጣ፤ ይህም ነገር አላስደሰተውም። እርሱም፥ “ለዳዊት ዐሥር ሺህ አሉለት፤ ለእኔ ግን ሺህ ብቻ! እንግዲህ መንግሥት እንጂ ሌላ ምን ቀረው!” አለ። 9 ከዚያች ዕለት አንሥቶ ሳኦል ዳዊትን በቅናት ዐይን ይመለከተው ጀመር። 10 በማግስቱም ከእግዚአብሔር የታዘዘ ክፉ መንፈስ ሳኦልን ተቆራኘው፥ ሳኦል በቤቱ ሆኖ እንደ እብድ ይለፈልፍ ነበር፤ በዚህ ጊዜ ዳዊት በየእለቱ እንደሚያደርገው ሁሉ በገና ሲደረድር ነበር። ሳኦል በእጁ ጦር ይዞ ነበር። 11 እርሱም፥ “ዳዊትን ከግድግዳው ጋር አጣብቀዋለሁ” ብሎ በማሰብ ጦሩን ወረወረበት፤ ዳዊት ግን ሁለት ጊዜ ከፊቱ ዘወር አለ። 12 ጌታ ከእርሱ ተለይቶ ከዳዊት ጋር ስለሆነ ሳኦል ዳዊትን ፈራው። 13 ስለዚህ ዳዊትን ከአጠገቡ በማራቅ የሺህ አለቃ አደረገው። ዳዊትም ሠራዊቱን እየመራ በፊታቸው ይወጣና ይገባ ነበር። 14 ጌታም ከእርሱ ጋር ስለ ነበር የሚያደርገው ነገር ሁሉ ይሳካለት ነበር። 15 ሳኦልም፥ ዳዊት እንደ ተሳካለት ባየ ጊዜ ከመቼውም ጊዜ በላይ ፈራው፤ 16 መላው እስራኤልና ይሁዳ ግን በፊታቸው እየወጣና እየገባ የሚመራቸው እርሱ ነበርና ዳዊትን ወደዱት። ዳዊት የሳኦልን ልጅ ማግባቱ17 ሳኦል ዳዊትን፥ “ታላቋ ልጄ ሜራብ እነኋት፤ እርሷን እድርልሃለሁ፤ አንተ ግን በጀግንነት አገልግለኝ፤ የጌታንም ጦርነቶች ተዋጋልኝ” አለው፤ ሳኦል በልቡ፥ “ፍልስጥኤማውያን እጃቸውን ያንሡበት እንጂ እኔ በእርሱ ላይ እጄን አላነሣም” ብሎ ነበር። 18 ዳዊት ግን ሳኦልን፥ “የንጉሥ ዐማች እሆን ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ቤተሰቤም ሆነ የአባቴ ወገን በእስራኤል ዘንድ ምንድነው?” አለው። 19 ይሁን እንጂ የሳኦል ልጅ ሜራብ ለዳዊት የምትዳርበት ጊዜ ሲደርስ ለመሓላታዊው ለኤድሪኤል ተዳረች። 20 በዚህ ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል ዳዊትን ወደደችው፤ ሳኦልም ይህን ሲሰማ ደስ አለው። 21 ሳኦልም በልቡ፥ “ወጥመድ እንድትሆነው፥ በፍልስጥኤማውያንም እጅ እንዲጠፋ እርሷን እድርለታለሁ” ሲል አሰበ። ስለዚህ ሳኦል ለሁለተኛ ጊዜ ዳዊትን፥ “እነሆ፤ ዛሬ ዐማቼ ትሆናለህ” አለው። 22 ከዚያም ሳኦል ባለሟሎቹን፥ “ለዳዊት፥ ‘እነሆ፤ ንጉሡ በአንተ ደስ ብሎታል፤ ባለሟሎቹም ሁሉ ይወዱሃል፤ ስለዚህ ዐማቹ ሁንለት’ ብላችሁ በምስጢር ንገሩት” ብሎ አዘዛቸው። 23 እነርሱም ይህንኑ ለዳዊት ደግመው ነገሩት፤ ዳዊት ግን “ለመሆኑ የንጉሥ ዐማች መሆንን እስከዚህ ትንሽ ነገር አድርጋችሁ ትቆጥራላችሁን? እኔ አንድ ምስኪን ድኻና እውቅና የሌለኝ መሆኔን አጣችሁትን?” አላቸው። 24 የሳኦል ባለሟሎችም ዳዊት ያላቸውን ነገሩት። 25 ሳኦልም፥ “ዳዊትን፥ ‘ንጉሡም ለልጅቱ ካንተ የሚፈልገው ጥሎሽ ጠላቶቹን ለመበቀል የመቶ ፍልስጥኤማውያንን ሸለፈት እንጂ ሌላ አይደለም ብላችሁ ንገሩት’ ” አላቸው። ሳኦል ይህን ያቀደው ዳዊት በፍልስጥኤማውያን እጅ እንዲወድቅ ነበር። 26 ባለሟሎቹ ይህን ለዳዊት በነገሩት ጊዜ የንጉሥ ዐማች መሆኑ ደስ አሰኘው። ስለዚህ የተወሰነው ጊዜ ከማለፉ በፊት፥ 27 ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎቹ ሄደው ሁለት መቶ ፍልስጥኤማውያንን ገደሉ፤ ለንጉሡ ዐማች ይሆን ዘንድ፥ ሸለፈታቸውን አምጥቶ በቁጥራቸው ልክ ለንጉሡ አቀረበ፤ ከዚያም ሳኦል ልጁን ሜልኮልን ለዳዊት ዳረለት። 28 ሳኦል፥ ጌታ ከዳዊት ጋር እንደ ሆነና ልጁ ሜልኮልም እንደወደደችው በተረዳ ጊዜ፥ 29 ሳኦል ከቀድሞው ይልቅ ዳዊትን ፈራው፤ እስከ ዕድሜ ልኩም ጠላቱ ሆነ። 30 የፍልስጥኤማውያን ጦር አዛዦች እንደ ወትሮው ሁሉ ለጦርነት ይወጡ ነበር፤ ዳዊትም ከቀሩት የሳኦል መኳንንት የበለጠ ድል አገኘ፤ ስሙም እጅግ የታወቀ ሆነ። |