ስምዖን የአይሁዶች መሪና ሊቀ ካህናት ስምዖን መሪነቱን ያዘ1 ትሪፎን ወደ ይሁዳ አገር ለመሄድና አገሩን ለማጥፋት ከፍ ያለ የጦር ሠራዊት ማከማቸቱን ስምዖን ሰማ። 2 ሕዝቡ በፍርሃት መንቀጥቀጡን ባዩ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣና ሕዝቡን አሰባሰበ፤ 3 እንዲህ ሲል አረጋጋቸው፦ “እኔና ወንድሞቼ የአባቴም ቤት ስለ ሕግጋትና ስለ ቤተ መቅደስ ብለን ያደረግነውን ሁሉ ታውቃላችሁ። 4 ስለዚህ ነው ወንድሞቼ ሁሉ ስለ እስራኤል የሞቱት እኔም ብቻዬን የቀረሁት። 5 ይህ ጊዜ የመከራ ጊዜ ቢሆንም እኔ ሕይወቴን የማዳን ሐሳብ የለኝም፤ እኔ ከወንድሞቼ ይበልጥ የተሻልሁ አይደለሁም፤ 6 ነገር ግን ሕዝቦቹ ሁሉ በጥላቻ ተነሣሥተው እኛን ለመደምሰስ ስለተባበሩብን እኔ ስለ ሕዝቤና ስለ ቤተ መቅደሱ ስለ ሚስቶቻችሁና ስለ ልጆቻችሁ እበቀላለሁ።” 7 ይህን ቃል በመስማት የሕዝቡ መንፈስ ተነሣሣ፤ 8 በታላቅ ድምፅ እንዲህ እያሉ መለሱለት፤ “በወንድሞችህ በይሁዳና በዮናታን ፈንታ አንተ መሪያችን ነህ፤ 9 ውጊያችንን ምራ፤ የምትለንን ሁሉ እንፈጽማለን”። 10 እርሱም የጦር ሰዎችን በሙሉ ሰበሰበ፤ የኢየሩሳሌምን ግንብ ሠርቶ ለመጨረስ ተጣደፈ፤ በዙሪያውም አጠናከረው። 11 የአቤሰሎም ልጅ ዮናታን በቂ ሠራዊት አስከትሎ ወደ ኢዮጴ እንዲሄድ አደረገው፤ ዮናታን ነዋሪዎቹን አባሮ እዚያው ተቀመጠ። ስምዖን ትሪፎንን ከይሁዳ አስወጣው12 ትሪፎን ከብዙ ሠራዊት ጋር ሆኖ ወደ ይሁዳ አገር ለመግባት ከጰጦሎማይዳ ተነሣ፤ ከእርሱ ጋር ምርኮኛውን ዮናታንን ይዞ ሄደ። 13 ስምዖን መጥቶ በሜዳው ፊት ለፊት በአዲዳ ሠፈረ። 14 ስምዖን በወንድሙ በዮናታን እግር ተተክቶ ሊዋጋው መዘጋጀቱን ባወቀ ጊዜ ትሪፎን እንዲህ ሲል መልእክተኞችን ላከበት፥ 15 “ወንድምህን ዮናታንን ይዘን ያቆየነው ለመንግሥት ሊከፍል በሚገባው ገንዘብ (ዕዳ) ምክንያት ነው፤ 16 አሁን አንድ መቶ የብር መክሊትና መያዢያ የሚሆኑ ሁለቱ ልጆቹን ላክልን፤ ይህንንም የምንለው ከተለቀቀ በኋላ እንዳይሸፈትብን ብለን ነው፤ ይህ ከተደረገልን እንለቀዋልን”። 17 ስምዖን ምንም እንኳ ይህ ቃል የአታላይነት ቃል መሆኑን ቢያውቅም ከሕዝቡ ታላቅ ጥላቻ እንዳይመጣበት በመፍራት ገንዘቡንና ልጆቹን አስመጣ፥ 18 “ዮናታን የሞተው ገንዘቡንና ልጆቹን ስላልላከለት ነው። ይሉኛል”። በሚል ፍራቻ የተጠየቀውን ሁሉ ላከለት። 19 ስለዚህ ነው ልጆቹንና መቶውን መክሊት የላከለት፤ ነገር ግን እንደገመተው አታለለው፤ ዮናታንንም አለቀቀውም። 20 ከዚህ በኋላ ትሪፎን ሀገሪቱን ለመውረርና ለማጥፋት ገሠገሠ፤ ወደ አዶራ በሚወስደው መንገድ ዞሮ ሄደ፤ ግን ስምዖንና የእርሱ ሠራዊት እርሱ በሄደበት ሁሉ እየተከታተሉ ይቃወሙት ነበር። 21 በዚያን ጊዜ በምሽጉ ውስጥ የነበሩት ሰዎች ቶሎ በበረሃው በኩል እንዲመጣላቸው፥ ስንቅም እንዲልክላቸው ወደ ትሪፎን መልእክተኞች ላኩ። 22 ትሪፎን ወደዚያ ለመሄድ ፈረሰኛ ጦሩን በሙሉ አዘጋጀ፤ ግን በዚያች ሌሊት ብዙ በረዶ ጣለ፤ ስለዚህ መሄድ አልቻለም፤ ከዚያ ተነሣና ወደ ገለዓድ አገር አመራ። 23 ወደ ባስካማ ሲቃረብ ዮናታንን ገደለው፤ በዚያም ተቀበረ። 24 ከዚህ በኋላ ትሪፎን ወደ አገሩ ተመለሰ። ዮናታን ስምዖን በሞዲን ባዘጋጀው መቃብር ተቀበረ25 ስምዖን ሰው ልኮ የወንድሙን ዓፅም አስመጣና በአባቶቹ ከተማ በመዲን አስቀበረው። 26 እስራኤል በመላው ታላቅ ኀዘን አደረጉለት፤ ለብዙ ቀናትም አለቀሱለት፤ 27 ስምዖን የአባቱና የወንድሞቹ መቃብር በሩቅ እንዲታዩ ብሎ በስተ ኋላውም፥ በስተ ፊቱም በጥርብ ድንጋይ ከፍ አድርጐ ሠራው። 28 ለአባቱ፥ ለእናቱ፥ ለአራቱ ወንድሞቹ ሰባት ሐውልቶችን አጠገብ ለአጠገብ አቆመ። 29 በዙሪያቸው በኪነጥበብ የተሠሩ ረዣዥም ዓምዶቹ ላይ በባሕር ላይ የሚሄዱ ሰዎች ሁሉ የሚያዩዋቸውን የዘለዓለም ማስታወሻ የሚሆኑ የጦር መሣሪያዎችና መርከቦች ተቀርጸውባቸው ነበረ። 30 በሞዲን የተሠራው እስከ ዛሬም የሚታየው መቃብር ይህ ነው። ዳግማዊ ዲሜጥሮስ ለስምዖን የዋለው ውለታ31 ትሪፎን በወጣቱ ንጉሠ በአንጥዮኩስ ላይ የአታላይነት ሥራ ሠርቶ ገደለው፤ 32 በምትኩ እርሱ ነገሠና የእስያን ዘውድ ተቀዳጀ፤ በአገሩ ላይም ታላቅ መከራ አወረደበት። 33 ስምዖን የይሁዳን አገር ምሽጐች እንደገና ሠራቸው፤ በዙሪያቸው ረዣዥም የግንብ ምሽጐችን ሠራ፤ መዝጊያዎችና መቆለፊያዎች ያሏቸው ታላላቅ መካባቢያዎችንም ሠራ፤ በምሽጐቹ ውስጥ ስንቅ አስገብቶ አስቀመጠ። 34 ከዚህ በኋላ ስምዖን ወደ ንጉሥ ዲሜጥሮስ ሰው ልኮ አገሩን ከግብር ነጻ እንዲያወጣ ጠየቀ ምክንያቱም ትሪፎን ከመዝረፍ በቀር ሌላ ያደረገው ነገር የለም። 35 ንጉሥ ዴሜጥሮስ እንዲህ ሲል መልሱን ጻፈለት፤ 36 “ንጉሥ ዲሜጥሮስ ለሊቀ ካህናትና ለነገሥታት ወዳጅ፤ ለስምዖን፥ ለሽማግሌዎችና ለአይሁድ ሕዝብ ሰላምታ ያቀርባል። 37 የላካችሁለንን የወርቅ ዘውድና ዘንባባ ተቀብለናል፤ ከእናንተ ጋር ፍጹም የሰላምታ ውል ለመዋዋልና ቀረጥም እንዳያስከፍሏቸሁ ለሠራተኞቻችን ለመጻፍ ዝግጁዎች ነን፤ 38 ልናደርግላችሁ የወሰንነው ነገር ሁሉ የጸና ይሆናል፤ የሠራችኋቸው ምሽጐችም የእናንተ ናቸው፤ 39 በማወቅም ሆነ ባለማወቅ እስከ ዛሬ የተደረገውን ስሕተትና በደል ይቅር ብላችኋል፤ መክፈል የሚገባችሁን የዘውድ ግብርና ከኢየሩሳሌም የሚከፈለውንም ሌላ ግብር ትተንላችኋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ አትገደዱም። 40 ከእናንተ መካከል አንዳንዶች ከወታደሮቻችን ጋር ተቀጥረው መሥራት የሚችሉ ካሉ ይመዝገቡ በመካከላችን ሰላም ይሁን”። 41 በመቶ ሰባ (27 ግንቦት 142) ዓመተ ዓለም የአረማውያን ቀንበር ከእስራኤል ተነሣ፤ 42 ሕዝቡም በጽሑፎቻቸውና በውሎቻቸው ላይ፥ “የአይሁድ ሕዝብ የጦር መሪና አለቃ፥ የሊቀ ካህናት ስምዖን መጀመሪያ ዓመት” እያሉ መጻፍ ጀመሩ። ስምዖን ጌዘርን ያዘ43 በእነዚያ ቀናት ስምዖን ጌዘርን ለመውጋት በሁሉም ቦታ በወታደሮቹ አስከበባት ተንቀሳቃሽ ማማ ሠራና ወደ ከተማው አስጠጋው፤ ከምሽጐቹ አንዱን መትቶ አፈራረሰና ያዘው። 44 በተንቀሳቃሽ ማማ ውስጥ የነበሩት ሰዎች እየዘለሉ ወደ ከተማው ገቡ፤ ትልቅ ሁከትም ተፈጠረ። 45 የከተማው ነዋሪዎች ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው በበመካበቢያው ግንብ ላይ ወጡ፤ ልብስሳቸውን ቀደዱ፤ ስምዖን ሰላምን እንዲፈጥርና እንዲሰጣቸው ለመኑት። 46 እንደክፋታችን አታድርግብን፥ እንደ ምሕረትህ አድርግልን አሉት። 47 ስምዖን ከእነርሱ ጋር አንድ ስምምነት አደረገና ጦርነቱን አቆመ፤ ነገር ግን ከከተማዋ አባረራቸው፤ ጣዖቶች የነበሩባቸውን ቤቶች አጸዳ፤ ከዚህ በኋላ በዜማና በምስጋና ገባ፤ 48 እርኩሱን ነገር ሁሉ አስወገደ፤ ሕግን ያከብሩ የነበሩትን ሰዎች እዚያ አስቀመጠ፤ ከተማዋን አጠናከረ፤ መኖሪያ ቤቱንም እዚያ ሠራ። በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ምሽግ ስምዖን ተቆጣጠረ49 በኢየሩሳሌም ምሽግ ውስጥ ያሉት ሰዎች ለመግዛትም ሆነ ለመሸጥ ወደ አገሩ ውስጥ መሄድና መምጣት ስላልቻሉ በረሃብ እጅግ ተሠቃዩ፤ በረሃብ ብዙ ሰዎች ሞቱ። 50 ሰላም እንዲያደርግና እንዲቀበላቸው ስምዖንን ለመኑት። እርሱም እሺ አላቸው፤ ቢሆነም ከቦታው አስወጣቸውና ምሽጉን ከእርኩስ ነገር አፀዳ። 51 ከሃያ ሦስተኛው ቀን በሁለተኛው ወር በመቶ ሰባ አንድ (ሰኔ 4 ቀን 141) ዓመተ ዓለም በእልልታና በዘንባባ፥ በመሰንቆና በጸናጽል፥ በክራር፥ በዝማሬና በማሕሌት ገቡ፤ ምክንያቱም አንድ ትልቅ ጠላት ከእስራኤል ተነቅሎ ስለወደቀ ነው። 52 ስምዖን ይህ ቀን በየዓመቱ በደስታ ይንዲከበር አዘዘ። በምሽጉ ጐን የሚገኘውን የቤተ መቅደሱን ኮረብታ አጠናከረ፤ እርሱም ከእርሱ ሰዎች ጋር እዚያው ተቀመጠ፤ 53 ስምዓን የእርሱ ልጅ ዮሐንስ ለሙሉ ሰውነት የደረሰ መሆኑን ባየ ጊዜ የጦሩ አዛዥ የሠራዊቱ ሁሉ አለቃ አድርጐ ሾመው፥ ተቀማጭነቱም በጌዜር ሆነ። |