1 በጎ ልቡናንና የሚጣፍጥ እህልን አይንቁትም፤ ለባለጸግነት መትጋት ፈጽሞ ሰውነትን ያከሳል፥ ገንዘብንም ማሰብ እንቅልፍን ያሳጣል። 2 የሚጠራጠሩትን ማሰብ በእንጉልቻ እንቅልፍን ያስረሳል፤ ከባድ ሕማምም ያተጋል፥ እንቅልፍንም ያሳጣል። 3 ባለጸጋ ገንዘብ ያደልብ ዘንድ ይዞራል፤ ባረፈም ጊዜ በጥጋብ ደስ ይለዋል። 4 ድሃ ገንዘብ በማጣት ይደክማል፤ ባረፈም ጊዜ ወደ ልመና ይመለሳል። 5 ገንዘብን የሚወድ ሰው አይጸድቅም፤ ኀጢአትንም የሚወዳት ሰው ይከተላታል። 6 ስለ ገንዘብ የወደቁ ሰዎች ብዙ ናቸው፤ ሞታቸውንም በፊታቸው አዩኣት። 7 ገንዘብ ለሚፈልጓት የእንቅፋት ዕንጨት ናት፤ ሰነፍ ሰው ሁሉ በእርስዋ ይሰነካከላል። 8 ከኀጢአት ንጹሕ የሆነ፥ ልቡናውንም ከገንዘብ በኋላ ያላስከተለ ባለጸጋ ብፁዕ ነው። 9 ለወገኖቹ መልካም ነገር የሚያደርግ ማንነው? እንጃ! እርሱን እናደንቀዋለን። 10 በእርሱ የተፈተነ፥ ያልሳተም እርሱም መመኪያ የሆነው ማን ነው? ኀጢአት መሥራት ሲቻለው ኀጢአት የማይሠራ ማን ነው? እንጃ። ክፉ መሥራት ሲቻለውስ ክፉ የማያደርግ ሰው ማን ነው? 11 በረከቱ ትጸናለች፤ ምጽዋቱም በአሕዛብ ሀገር ትሰማለች። የማዕድ ሥርዐት12 በታላቅ ማዕድም ብትቀመጥ ለመብላት ጉሮሮህን አትክፈት፤ ምግቡም ምን ያህል ነው ብለህ አታጋን፤ 13 የሰው ዐይን ክፉ እንደ ሆነ አስብ፤ ከሰው ዐይን የሚከፋ ምን አለ? ስለዚህም ነገር ዐይን ታለቅሳለች። 14 ላየኸው ሁሉ አትሳሳ፤ እጅህን አትንከር፤ ወጭቱን ወደ አንተ አትጎትት፥ ድስቱንም አትጥረግ። 15 ባልንጀራህ የጋበዘህን ዕወቅ፤ ያቀረበልህንም ሁሉ ተረዳ። 16 ያቀረቡልህን እንደ ብልህ ሰው ሁነህ ብላ፤ ባልንጀራህን እንዳታስጸይፍ ስታላምጥ ምላስህን አታጩህ። 17 እንደ ብልህ ሰው ሁሉ አስቀድመህ ተው፤ አትሳሳ፤ እንደማይጠግብ ሰውም አትሁን። 18 በብዙዎች መካከልም ብትቀመጥ እጅህን አስቀድመህ አትስደድ። 19 በመኝታህ ሆድህን እንዳይከብድህ፥ ጥቂት እንደሚበቃው እንደ ዐዋቂ ሰው መጥነህ ብላ። 20 መጥኖ የሚመገብ ሰው እንቅልፉ ጤና ነው፤ ከእንቅልፉም በጧት በነቃ ጊዜ ሆዱን አይከብደውም፤ ለማይጠግብ ለስሱ ሰው በሽታው ቍንጣን፥ ጓታና ብስና ነው። 21 ትበላ ዘንድ ግድ ቢሉህ ቀድመሃቸው ተነሥ፤ ከመብላትም ዕረፍ። 22 ልጄ ሆይ አድምጠኝ፤ ምክሬንም አትናቅ፤ ኋላ ነገሬን ታገኘዋለህ፤ ምንም እንዳታጣ በምትሠራው ሥራ ሁሉ ደካማ አትሁን። 23 ለጋስን ሰው በሥራው ማማር ይመርቁታል፤ የደግነቱ ምስክርነትም የታመነ ነው፤ ንፉግ ሰውንም በክፉ ሥራው ይረግሙታል። የክፋቱ ምስክርነትም የተረዳ ነው። 24 መጠጥ ብዙ ሰዎችን አስትዋቸዋልና፥ ወይን በጠጣህ ጊዜ አትታበይ። 25 ጽኑ ብረትን በወናፍ ይፈትኑታል፤ እንዲሁም ሁሉ የትዕቢተኞችን ልቡና ወይን ይፈትነዋል። 26 የሰው ሕይወቱ ወይን መጠጣት ነው፤ መጥኖ ለሚጠጣውም ሰው ደስታ ነው፤ እርሱ ለሰው ደስታ ሊሆን ተፈጥሯልና ወይን ለማይጠጣ ሰው ሕይወቱ ምንድን ነው? 27 ለልብ ደስታ ነው፤ ለሰውነትም ሐሤት ነው፤ ወይንን መጥኖ በጊዜው መጠጣት መልካም ነው። 28 ወይን የልቡና ኀዘንን ያስረሳል፤ ለሚያለቅስና ለሚያዝን ሰውም ወይንን አጠጣው። 29 ሰነፍ ሰው ወይን በጠጣ ጊዜ ክርክርን ያበዛል፥ ይስታል፥ ይበድላልም፤ የመጠጥ ብዛት ኀይልን አያስገኝም፤ ቍስልንም አያሳጣም። 30 ወይን ጠጥቶ ሳለ ባልንጀራህን አትቈጣው፤ ልቡ ደስ ብሎት ሳለም አታሳዝነው፤ የምትነቅፈውንም አትንገረው፤ እርሱ ሰክሮ ሳለ ጉዳይህን አትለምነው፤ አትዘብዝበውም። |