ስለ ልጆች1 ልጁን የሚወድ ሰው በፍጻሜው በእርሱ ደስ ይለው ዘንድ፥ ልጁን መቅጣትን ቸል አይልም። 2 ልጁን የሚቀጣ ሰው በእርሱ ደስ ይለዋል፤ በወዳጆቹም ዘንድ ይመካበታል። 3 ልጁን ያስተማረ ሰው ጠላቱን ያስቀናል፥ በወዳጆቹም ዘንድ በእርሱ ደስ ይለዋል። 4 ከእርሱ በኋላ እንደ እርሱ ያለ ልጅ ተክትዋልና አባቱ ቢሞትም እንዳልሞተ ይሆናል። 5 በሕይወቱም ሳለ በልጁ ደስ ይለዋል፤ ቢሞትም ልቡ አያዝንም። 6 ከእርሱ በኋላ ጠላቶቹን የሚበቀል፥ ለወዳጆቹም ዋጋን የሚከፍል ልጅ ተክትዋልና። 7 ልጆቹን የሚያባልግ ሰውነቱ ይቈስላል፤ በጩኸታቸውም ጊዜ ልቡ በሕመም ይሠቃያል። 8 ያልተገራ ፈረስ ገርጋሪ ይሆናል፤ ያልተቀጣ ልጅም አውታታ ይሆናል፤ 9 ልጅህን ካቀማጠልኸው ይበረታታብህ ዘንድ ይመለሳል፤ ከእርሱም ጋር ብትጫወት ያሳዝንህ ዘንድ ይመለሳል። 10 እንዳያሳዝንህም አትሳቅለት፤ በፍጻሜም ጥርስህን ያረግፍሃል። 11 በወጣትነቱ ጊዜ ልጅህን ስድ አትልቀቀው። በስሕተቱም ጊዜ ቸል አትበለው፤ 12 በአደገ ጊዜ እንዳያምፅብህ በልጅነቱ ጊዜ ጎኑን ግረፈው። 13 በእርሱ ጥፋት እንዳታፍር ልጅህን ቅጣው፤ ያገለግልሃልም። ስለ ጤንነት14 ሰውነቱ ከታመመና ሆዱ ከታሰረ ባለጸጋ፥ ሰውነቱ ጤነኛ የሆነና ሆዱ የተከፈተ ድሃ ይሻላል። 15 ሰውነትህ ጤነኛ ይሁን፤ ሆድህም የተከፈተ ይሁን፤ ይህም ከባለጸግነት ሁሉ ይሻላል። ከባለጸግነትና ከገንዘብም ሁሉ የሰውነት ጤንነት ይሻላል። 16 በጤና ከመኖር ባለጸግነት አይመረጥም፤ ከልብ ደስታም የሚሻል ደስታ የለም። 17 ከመረረ ኑሮና ከቍርጥማት በሽታ ሞት ይሻላል። 18 በተዘጋ አፍ የሚቀርብ መብል ወደ መቃብር እንደሚወሰድ እህል ነው። 19 ለጣዖታት መሠዋት ምን ይጠቅማል? እነርሱ አይበሉምና፥ እነርሱም አይጠጡምና፥ እነርሱም አያሸትቱምና፥ እግዚአብሔር የቀሠፈውም ሰው እንደዚሁ ነው። 20 ጃንደረባ ቆንጆዪቱን ባቀፋት ጊዜ እንደሚያዝን፥ በዐይኖቹ እያየ ያዝናል። 21 ነፍስህን አታሳዝን፤ ልብህንም አታስጨንቅ። 22 የልቡና ደስታ ለሰው ሕይወቱ ነው፤ የሰውነት ደስታም ዘመንን ያረዝማል። 23 ኀዘንን ከአንተ ታርቃት ዘንድ ልብህን አጽናናት፤ ሰውነትህንም አረጋጋት፤ ኀዘን ብዙ ሰዎችን አጥፍታቸዋለችና፤ ኀዘንም የምትጠቅመው የለምና። 24 ቅናትና ቍጣ የሕይወት ዘመንን ያሳንሳሉ፤ ኀዘንም ጊዜው ሳይደርስ ያስረጃል። 25 አጫጅን እየተከተለ እንደሚቃርም ሰው፤ በእግዚአብሔር በረከት ደረስሁ። እንደ ወይን ለቃሚም መጭመቂያዬን ሞላሁ። 26 ጠቢባን ይሆኑ ዘንድ ለሚወዱ ሰዎችም ሁሉ ነው እንጂ፥ የደከምኩ ለእኔ ብቻ እንዳይደለ እነሆ አስተውሉ። 27 የሕዝቡ መኳንንት ስሙኝ፥ የማኅበሩም አለቆች አድምጡኝ። 28 ልጅህንና ሚስትህን፥ ወንድምህንና ወዳጅህን አንተ በሕይወት ሳለህ፥ በገንዘብህ ላይ አታሠልጥናቸው ኋላ እንዳትጸጸት፥ ትለምናቸውም ዘንድ እንዳትመለስ፥ በቤትህ ባዕድ ሰው አትሹም። 29 አንተ በሕይወት ሳለህ፥ ትንፋሽህም ሳለች ግብርህን አትለውጥ። 30 አንተ የልጆችህን እጅ ደጅ ከምትጠና፤ ልጆችህ አንተን ቢለምኑህ ይሻልሃል። 31 በምትሠራው ሥራ ሁሉ ብልህ ሁን፤ በተሾምህበትም ሁሉ ራስህን አታስነቅፍ። 32 የሕይወት ዘመንህ ሁሉ በአለቀ ጊዜ፤ ፍጻሜህም በደረሰ ጊዜ፥ ያን ጊዜ ገንዘብህን አውርስ። 33 አህያህን ገለባ አብላው፤ ጫነው፤ በአለንጋም ግረፈው፤ አገልጋይህንም ቅጣው፤ መግበው፤ ግዛውም። 34 አገልጋዮችህንም እንዲሠሩ አድርጋቸው፤ ዕረፍትንም ታገኛለህ፤ ብታቦዝናቸው ግን ይከራከሩህ ዘንድ፥ ከአንተም ነጻ ይወጡ ዘንድ ይወድዳሉ። 35 ቀንበር መጫን አንገትን ዝቅ ያደርገዋል፤ አለንጋና እግር ብረትም ለክፉ አገልጋይ ነው። 36 አገልጋይህን እንዲሠራ አድርገው፥ አቦዝነህ አታኑረው። 37 ቦዘኔነት ብዙ ክፋትን ታስተምራለችና። 38 የሚችለውን ያህል ሥራውን ስጠው፤ ባይታዘዝ ግን እግር ብረቱን አጽናበት፤ ነገር ግን ሥጋዊውን ሁሉ አትመነው። ያለ ምክርም የምትሠራው ሥራ አይኑር፤ 39 አገልጋይ ቢኖርህ እንደ ራስህ ይሁን፤ በዋጋ ገዝተኸዋልና፥ ደግ አገልጋይም ቢኖርህ እንደ ወንድምህ አድርገው፤ እንደ ራስህም ውደደው። 40 ክፉ ነገር ብታደርግበት ግን ይኰበልልብሃል፤ ያመልጥሃልም፤ ከዚህ በኋላ በየት ጎዳና ታገኘዋለህ? |