1 እግዚአብሔርን ለሚታገሥ ሰው ይበቀልለታል፤ ኀጢአቱንም ያስተሰርይለታል። 2 ባልንጀራህ የበደለህን በደል ይቅር በለው፥ የዚያን ጊዜ ንስሓ ከገባህ ኀጢአትህን ያስተሰርይልሃል። 3 አንተ ሰው ስትሆን እንደ አንተ ያለውን ሰው ከተቀየምህ፥ እግዚአብሔርን እንዴት ይቅር በለኝ ትለዋለህ? 4 እንደ አንተ ያለ ሰውን ይቅር ሳትል፥ ኀጢአትህን ያስተሰርይልህ ዘንድ እንግዲህ እንዴት ትለምነዋለህ? 5 ሥጋ ለባሹ ቂመኛ ከሆነ ኀጢአቱን ማን ያስተሰርይለታል? 6 ፍጻሜህን ዐስበህ ጠብን ተዋት። ሞትንና ሙስና መቃብርን ዐስብ፤ ትእዛዙንም ጠብቅ። 7 ሕጉን ዐስበህ ባልንጀራህን አትቀየም፤ የልዑልን ፍርዱን ዐስበህ ቍጣን አርቃት። 8 ኀጢአቶችህን ታሳንስልህ ዘንድ ክርክርን ተዋት፤ ቍጡ ሰው ክርክርን ያነሣሣል። 9 ኀጢአተኛ ሰውም ባልንጀራውን ያደክማል፤ ወዳጆቹንም ያጣላል። 10 በእንጨቱ ልክ የእሳቱ ነዲድ ይበዛል፤ በክርክሩም ብዛት መጠን ጠቡ ይበዛል፤ የሰው ኀይሉ በቁመቱ መጠን ነው፤ በባለጸግነቱም ብዛት መጠን ቍጣውን ያበዛታል። 11 መታበይን የሚያበዛት ሰው እሳትን ያቀጣጥላታል፤ ለጠብ የሚቸኵል ሰውም ፈጥኖ ደምን ያፈስሳል። ክፉ ምላስ12 ፍምን እፍ ብትላት ትነድዳለች፤ ትፍ ብትልባትም ትጠፋለች፤ ሁለቱም ከአንድ አፍ ይወጣሉ። 13 ሐሜተኛንና ሁለት አንደበት ያለውን ሰው ይረግሙታል፤ ብዙ ወዳጆችን አጋድሎአልና። 14 ነገረ ሠሪ አንደበት ብዙ ሰዎችን አወካቸው፤ ከሕዝብም ወደ ሕዝብ አሳደዳቸው። የጸኑ ከተሞችንም አፈረሰ፤ የመኳንንቱንም ቤት ጣለ። 15 ቀባጣሪ አንደበት ደጋግ ሴቶችን ከባሎቻቸው ቤት አስወጥታ ሰደደቻቸው፤ ገንዘባቸውንም አጠፋችባቸው። 16 ከእርስዋ ያልተጠበቀ ሰው ግን ለዘለዓለሙ አያርፍም፤ በሰላምም አይኖርም። 17 የግርፋት ቍስል መግል ይይዛል፤ የአንደበት ቍስል ግን አጥንትን ይሰብራል። 18 በጦር የወደቁ ሰዎች ብዙ ናቸው፤ ነገር ግን በአንደበት እንደ ጠፉ አይደሉም። 19 ከእርሷ የዳነና በጥፋትዋ ያልተሰነካከለ፥ በቀንበሯም ያላረሰ፥ በእግር ብረትዋም ያልታሰረ ብፁዕ ነው። 20 ቀንበርዋ የብረት ቀንበር ነውና፤ እግር ብረቷም የብርት ነውና። 21 ሞትዋም ክፉ ሞት ነው፤ ከእርስዋም ሲኦል ትቀላለች። 22 በጻድቃን ግን አትደርስባቸውም፤ በእሳቷም አይቃጠሉም። 23 እግዚአብሔርን የዘነጉ ሰዎች በእርስዋ ይወድቃሉ፤ በማይጠፋ እሳትዋም ታቃጥላቸዋለች። እንደ አንበሳም ትወረወርባቸዋለች፤ እንደ ነብርም ትይዛቸዋለች። 24 ንብረትህን በእሾህ ብታጥር፥ ወርቅህንና ብርህንም ብትቈልፍ፥ 25 ነገርህን በሚዛን ብትመዝን፥ ለአፍህም መዝጊያና ቍልፍ ብታደርግ፥ 26 ዳግመኛም በአንደበትህ እንዳትሰነካከል፥ በሚያድንህም ፊት እንዳትጥልህ ተጠበቅ። |