ብልጣሶር ለመኳንንቱ ግብር እንደ አበላ1 ንጉሡ ብልጣሶር ለሺህ መኳንንቱ ትልቅ ግብዣ አደረገ፤ ለሺሁም የወይን ጠጅ ያጠጣ ነበር። 2 ብልጣሶርም የወይን ጠጅ በጠጣ ጊዜ ንጉሡና መኳንንቱ፥ ሚስቶቹና ቁባቶቹ ይጠጡባቸው ዘንድ፥ “አባቴ ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ከነበረው ቤተ መቅደስ ያመጣቸውን የወርቁንና የብሩን ዕቃዎች አምጡ” ብሎ አዘዘ። 3 ያን ጊዜም በኢየሩሳሌም ከነበረው ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የመጡትን የወርቁንና የብሩን ዕቃዎች አመጡ፤ ንጉሡና መኳንንቱም፥ ሚስቶቹና ቁባቶቹም ጠጡባቸው። 4 የወይን ጠጅም እየጠጡ ከወርቅና ከብር፥ ከናስና ከብረት፥ ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩትን አማልክት አመሰገኑ። 5 በዚያም ሰዓት የሰው እጅ ጣት ወጥታ በንጉሡ ቤት በተለሰነው ግንብ ላይ በመቅረዙ አንጻር ጻፈች፤ ንጉሡም የሰው ጣት ስትጽፍ አየ። 6 ያን ጊዜም የንጉሡ ፊት ተለወጠ፤ ልቡም ታወከ፤ የወገቡም ጅማቶች ተፈቱ፤ ጕልበቶቹም ተብረከረኩ። 7 ንጉሡም አስማተኞቹንና ከለዳውያኑን፥ ቃላተኞቹንም ያገቡ ዘንድ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ንጉሡም የባቢሎንን ጠቢባን፥ “ይህን ጽሕፈት ያነበበ፥ ፍቺውንም የነገረኝ ሐምራዊ ግምጃ ይለብሳል፤ የወርቅም ማርዳ በአንገቱ አስርለታለሁ፤ በመንግሥቴም ላይ ሦስተኛ ገዥ አድርጌ እሾመዋለሁ” ብሎ ተናገረ። 8 የዚያን ጊዜም የንጉሡ ጠቢባን ሁሉ ገቡ፤ ነገር ግን ጽሕፈቱን ያነብቡ ዘንድ፥ ፍቺውንም ለንጉሡ ይነግሩ ዘንድ አልቻሉም። 9 ንጉሡም ብልጣሶር እጅግ ደነገጠ፤ ፊቱም ተለወጠበት፤ መኳንንቱም ተደናገጡ። 10 ንግሥቲቱም የንጉሡንና የመኳንንቱን ቃል ሰምታ ወደ ግብዣ ቤት ገባች፤ እንዲህም አለች፥ “ንጉሥ ሆይ! ለዘለዓለም ኑር፤ አሳብህ አያስቸግርህ፤ ፊትህም አይለወጥ። 11 የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ ያለበት ሰው በመንግሥትህ ውስጥ አለ፤ በአባትህም ዘመን እንደ አማልክት ጥበብ ያለ ጥበብና ማስተዋል፥ ዕውቀትም ተገኘበት፤ አባትህ ንጉሡ ናቡከደነፆር የሕልም ተርጓሚዎችና የአስማተኞች፥ የከለዳውያንና የቃላተኞች አለቃ አድርጎ ሾመው። 12 መልካም መንፈስ፥ ዕውቀትም፥ ማስተዋልም፥ ሕልምንም መተርጐም፥ እንቆቅልሽንም መግለጥ፥ የታተመውንም መፍታት በእርሱ ተገኝቶአልና፤ እርሱም ንጉሡ ስሙን ብልጣሶር ብሎ የሰየመው ዳንኤል ነው። አሁንም እርሱ ይጠራ፤ እርሱም ፍቺውን ይነግርሃል።” 13 የዚያን ጊዜም ዳንኤል ወደ ንጉሡ ፊት ገባ፤ ንጉሡም ተናገረው፤ ዳንኤልንም እንዲህ አለው፥ “ንጉሡ አባቴ ከይሁዳ ከማረካቸው ከይሁዳ ምርኮኞች ልጆች የሆንህ ዳንኤል አንተ ነህን? 14 የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ እንደ አለብህ፥ ዕውቀትና ማስተዋልም፥ ሕልምንም መተርጐም እንደ ተገኘብህ ስለ አንተ ሰምቻለሁ። 15 አሁንም ይህን ጽሕፈት ያነብቡ ዘንድ፥ ፍቺውንም ይነግሩኝ ዘንድ ጠንቋዮችና ፈላስፎች፥ ጠቢባንና ሟርተኞችም ወደ እኔ ገብተው ነበር፤ ነገር ግን የነገሩን ፍቺ ይነግሩኝ ዘንድ አልቻሉም። 16 አንተ ግን ፍቺን ትሰጥ ዘንድ፥ የታተመውንም ትፈታ ዘንድ እንድትችል ሰምቻለሁ፤ አሁንም ጽሕፈቱን ታነብብ ዘንድ፥ ፍቺውንም ትነግረኝ ዘንድ ብትችል፥ ሐምራዊ ግምጃ ትለብሳለህ፤ የወርቅም ማርዳ በአንገትህ ዙሪያ አስርልሃለሁ፤ አንተም በመንግሥቴ ላይ ሦስተኛ ገዥ ትሆናለህ።” 17 የዚያን ጊዜም ዳንኤል መለሰ፤ በንጉሡም ፊት እንዲህ አለ፥ “ስጦታህ ለአንተ ይሁን፤ የመንግሥትህንም ሢሶ ለሌላ ስጥ፤ ነገር ግን ጽሕፈቱን ለንጉሡ አነብባለሁ፤ ፍቺውንም እነግርሃለሁ። 18 ንጉሥ ሆይ! ልዑል አምላክ ለአባትህ ለናቡከደነፆር መንግሥትንና ታላቅነትን፥ ክብርንና ግርማን ሰጠው። 19 ስለ ሰጠው ታላቅነት ወገኖችና አሕዛብ፥ በልዩ ልዩም ቋንቋ የሚናገሩ ሁሉ በፊቱ ይንቀጠቀጡና ይፈሩ ነበር፤ የፈቀደውን ይገድል፥ የፈቀደውንም በሕይወት ያኖር ነበር፤ የፈቀደውንም ያነሣ፥ የፈቀደውንም ያዋርድ ነበር። 20 ልቡ ግን በታበየ ጊዜ፥ በኵራትም ያደርግ ዘንድ መንፈሱ በጠነከረ ጊዜ፥ ከመንግሥቱ ዙፋን ተዋረደ፤ ክብሩም ተለየው። 21 ልዑል አምላክም የሰዎችን መንግሥት እንዲገዛ፥ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስኪያውቅ ደረስ ከሰው ልጆች ተለይቶ ተሰደደ፥ ልቡም እንደ አውሬ ልብ ሆነ፤ መኖሪያውም ከምድረ በዳ አህዮች ጋር ነበረ፤ እንደ በሬም ሣር በላ፤ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ። 22 ብልጣሶር ሆይ! አንተ ልጁ ስትሆን በእግዚአብሔር ፊት ልብህን አላዋረድህም፤ ይህንም ሁሉ አላወቅህም። 23 በሰማይ አምላክ በእግዚአብሔር ላይ ኰራህ፤ የመቅደሱንም ዕቃዎች በፊትህ አመጡ፤ አንተም መኳንንትህም፥ ሚስቶችህም፥ ቁባቶችህም የወይን ጠጅ ጠጣችሁባቸው፤ ከብርና ከወርቅም፥ ከናስና ከብረትም፥ ከእንጨትና ከድንጋይም የተሠሩትን፥ የማያዩትንና የማይሰሙትንም፥ የማያውቁትንም አማልክት አመሰገንህ፤ ትንፋሽህንና መንገድህን ሁሉ በእጁ የያዘውን አምላክ ግን አላመሰገንኸውም። 24 ስለዚህም ይህ የሰው እጅ ጣት ከእርሱ ዘንድ ተልኳል፤ ይህም ጽሕፈት ተጽፎአል። 25 “የተጻፈውም ጽሕፈት፦ ማኔ፥ ቴቄል፥ ፋሬስ ይላል። 26 የነገሩም ፍቺ ይህ ነው፤ ማኔ ማለት፥ እግዚአብሔር መንግሥትህን ቈጠራት፤ ፈጸማትም ማለት ነው። 27 ቴቄል ማለት፥ በሚዛን ተመዘነች፤ ቀልላም ተገኘች ማለት ነው። 28 ፋሬስ ማለት፥ መንግሥትህ ተከፈለች፤ ለሜዶንና ለፋርስ ሰዎችም ተሰጠች” ማለት ነው። 29 የዚያን ጊዜም ብልጣሶር ለዳንኤል ሐምራዊ ግምጃ እንዲያለብሱት፥ የወርቅ ማርዳም በአንገቱ ዙሪያ እንዲያደርጉለት አዘዘ፤ በመንግሥትም ላይ ሦስተኛ ገዥ እንዲሆን ዐዋጅ አስነገረ። 30 በዚያም ሌሊት የከለዳውያን ንጉሥ ብልጣሶር ተገደለ። 31 ሜዶናዊውም ዳርዮስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። ዕድሜውም ስድሳ ሁለት ዓመት ነበረ። |