ዳንኤልና ሠለስቱ ደቂቅ በናቡከደነፆር ቤተ መንግሥት1 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ከበባት። 2 እግዚአብሔርም የይሁዳን ንጉሥ ኢዮአቄምን፥ ከእግዚአብሔርም ቤት ዕቃ ከፍሎ በእጁ አሳልፎ ሰጠው፤ እርሱም ወደ ሰናዖር ምድር ወደ ጣዖቱ ቤት ወሰደው፥ ዕቃውንም ወደ ጣዖቱ ግምጃ ቤት አገባው። 3 ንጉሡም ለጃንደረቦቹ አለቃ ለአስፋኒዝ፦ ከተማረኩት ከእስራኤል ልጆች ከነገሥታቱና ከመሳፍንቱ ዘር፥ 4 ነውር የሌለባቸውንና መልከ መልካሞቹን፥ በጥበብ ሁሉ የሚያስተውሉትን፥ ዕውቀትም የሞላባቸውን፥ አስተዋዮች የሆኑትን፥ በንጉሡም ቤት መቆም የሚችሉትን ብላቴኖች ያመጣና የከለዳውያንንም ትምህርትና ቋንቋ ያስተምሩአቸው ዘንድ ነገረው። 5 ንጉሡም ሦስት ዓመት ያሳድጉአቸው ዘንድ፥ ከዚያም በኋላ በንጉሡ ፊት ይቆሙ ዘንድ ከንጉሡ ማዕድ፥ ከሚጠጣውም ጠጅ በየዕለቱ ድርጎአቸውን አዘዘላቸው። 6 ከእነዚህም መካከል ከይሁዳ ልጆች ዳንኤልና አናንያ ሚሳኤልና አዛርያ ነበሩ። 7 የጃንደረቦቹም አለቃ ስማቸውን ለውጦ፤ ዳንኤልን ብልጣሶር፥ አናንያንም ሲድራቅ፥ ሚሳኤልንም ሚሳቅ፥ አዛርያንም አብደናጎ ብሎ ጠራቸው። 8 ዳንኤልም ከንጉሡ ማዕድ እንዳይበላ፥ ከሚጠጣውም ጠጅ እንዳይጠጣ በልቡ ጨከነ፤ እንዳያበላውም የጃንደረቦቹን አለቃ ለመነው። 9 እግዚአብሔርም በጃንደረቦቹ አለቃ ፊት ለዳንኤል ሞገስንና ምሕረትን ሰጠው። 10 የጃንደረቦቹም አለቃ ዳንኤልን፥ “መብሉንና መጠጡን ያዘዘላችሁን ጌታዬን ንጉሡን እፈራለሁ፤ በዕድሜ እንደ እናንተ ከአሉ ብላቴኖች ይልቅ ፊታችሁ ከስቶ ያየ እንደ ሆነ፥ ከንጉሡ ዘንድ በራሴ ታስፈርዱብኛላችሁ” አለው። 11 ዳንኤልም የጃንደረቦቹ አለቃ በዳንኤልና በአናንያ፥ በሚሳኤልና በአዛርያ ላይ የሾመውን አሚሳድን፦ 12 “እኛን አገልጋዮችህን ዐሥር ቀን ያህል ፈትነን፤ የምንበላውንም ጥራጥሬ፥ የምንጠጣውንም ውኃ ይስጡን፤ 13 ከዚያም በኋላ የእኛን ሰውነትና ከንጉሡ ማዕድ የሚበሉትን የብላቴኖችን ሰውነት ተመልከት፤ እንደ አየኸውም ሁሉ ከአገልጋዮችህ ጋር የወደድኸውን አድርግ” አለው። 14 ይህንም ነገራቸውን ሰምቶ ዐሥር ቀን ፈተናቸው። 15 ከዐሥር ቀንም በኋላ ከንጉሡ ማዕድ ከበሉ ብላቴኖች ሁሉ ይልቅ ሰውነታቸው አምሮ፥ ሥጋቸውም ወፍሮ ታየ። 16 አሚሳድም መብላቸውንና የሚጠጡትን ጠጅ አስቀርቶ ጥራጥሬውን ሰጣቸው። 17 ለእነዚህም ለአራቱ ብላቴኖች እግዚአብሔር በትምህርትና በጥበብ ሁሉ ዕውቀትንና ማስተዋልን ሰጣቸው፤ ዳንኤልም በራእይና ሕልምን በመተርጐም ሁሉ አስተዋይ ነበረ። 18 እነርሱ ይገቡ ዘንድ ንጉሡ ያዘዘው ቀን በተፈጸመ ጊዜ፥ የጃንደረቦቹ አለቃ ወደ ናቡከደነፆር አገባቸው። 19 ንጉሡም በአነጋገራቸው ጊዜ ከብላቴኖቹ ሁሉ እንደ ዳንኤልና እንደ አናንያ እንደ ሚሳኤልና እንደ አዛርያ ያለ አልተገኘም፤ በንጉሡም ፊት ቆሙ። 20 ንጉሡም በጠየቃቸው ጊዜ በጥበብና በማስተዋል ነገር ሁሉ፥ በግዛቱ ሁሉ ከሚኖሩ የሕልም ተርጓሚዎችና አስማተኞች ሁሉ እነርሱ ዐሥር እጅ የበለጡ ሆነው አገኛቸው። 21 ዳንኤልም እስከ ንጉሡ እስከ ቂሮስ መጀመሪያ ዓመተ መንግሥት ተቀመጠ። |