የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ

ማስታወቂያዎች

መላው መጽሐፍ ቅዱስ ብሉይ ኪዳን አዲስ ኪዳን


ዘኍል 24 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)
ዘኍል 24

የበለዓም ሦስተኛው ትንቢት

1 በለዓምም ጌታ እስራኤልን መባረክ ደስ እንደሚያሰኘው ባየ ጊዜ፥ አስቀድሞ ያደርግ የነበረውን አስማት ለመሻት አልሄደም፤ ነገር ግን ወደ ምድረ በዳ ፊቱን አቀና።

2 በለዓምም ዓይኑን አንሥቶ እስራኤል በየነገዱ ተቀምጦ አየ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ መጣ።

3 እርሱም ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፦ “የቢዖር ልጅ በለዓም እንዲህ ይላል፥ ዐይኖቹ የተከፈቱለት ሰው እንዲህ ይላል፤

4 የእግዚአብሔርን ቃላት የሚሰማ፥ ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥ ወድቆም ሳለ ዐይኖቹ ግን የተከፈቱለት እንዲህ ይላል፦

5 ያዕቆብ ሆይ! ድንኳኖችህ፥ እስራኤል ሆይ! ማደሪያዎችህ ምንኛ ያምራሉ!

6 ወደፊትም ተዘርግቶ እንዳለው ሸለቆች፥ በወንዝ ዳር እንዳሉ አትክልቶች፥ ጌታ እንደ ተከለው ዓልሙን በውኃም ዳር እንዳሉ ዝግባዎች ተዘርግተዋል።

7 ከማድጋዎቹ ውኃ ይፈስሳል፥ ዘሩም በብዙ ውኆች ይሆናል፥ ንጉሡም ከአጋግ ይልቅ ከፍ ከፍ ይላል፥ መንግሥቱም ይከበራል።

8 እግዚአብሔርም ከግብጽ አውጥቶታል፤ ጉልበቱ አንደ ጎሽ ቀንድ ያለ ነው፤ ጠላቶቹን አሕዛብን ይበላል፥ አጥንቶቻቸውንም ይሰባብራል፥ በፍላጾቹም ይወጋቸዋል።

9 እንደ አንበሳ ዐርፎ ተኝቶአል፥ እንደ እንስቲቱም አንበሳ ተጋድሞአል፤ ማን ያስነሣዋል? የሚባርክህ ሁሉ የተባረከ ይሁን፥ የሚረግምህም ሁሉ የተረገመ ይሁን።”

10 የባላቅም ቁጣ በበለዓም ላይ ነደደ፤ እጆቹንም አጨበጨበ፤ ባላቅም በለዓምን እንዲህ አለው፦ “ጠላቶቼን እንድትረግምልኝ ጠራሁህ፥ እነሆም፥ ሦስት ጊዜ ፈጽመህ ይኸው ባረክሃቸው፤

11 እንግዲህ አሁን ወደ ስፍራህ ሽሽ፤ እኔም እንዲህ አልሁ፦ ‘በእውነት አከብርህ ዘንድ ወድጄ ነበር፤’ ጌታ ግን፥ እነሆ፥ ክብርህን ከለከለህ።”

12 በለዓምም ባላቅን እንዲህ አለው፦ “አንተ ወደ እኔ ለላክሃቸው መልእክተኞችህ እንዲህ ብዬ ነግሬአቸው አልነበረምን?

13 ‘ባላቅ በቤቱ የሞላውን ብርና ወርቅ ቢሰጠኝ፥ በራሴ ፈቃድ መልካምን ወይም ክፉን ነገር ለማድረግ የጌታን ቃል መተላለፍ አልችልም፤ ጌታ የተናገረውን እርሱን እናገራለሁ።’

14 እነሆ፥ አሁን፥ ወደ ሕዝቤ እሄዳለሁ፤ ና፥ ይህ ሕዝብ በሚመጣው ዘመን በሕዝብህ ላይ የሚያደርገውን እነግርሃለሁ።”

የበለዓም አራተኛው ትንቢት

15 እርሱም ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፦ “የቢዖር ልጅ በለዓም እንዲህ ይላል፥ ዐይኖቹ የተከፈቱለት ሰው እንዲህ ይላል፤

16 የጌታን ቃላት የሚሰማ፥ የልዑልንም እውቀት የሚያውቅ፥ ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥ ወድቆ ሳለ ዐይኖቹ ግን የተከፈቱለት እንዲህ ይላል፦

17 አየዋለሁ፥ አሁን ግን አይደለም፤ እመለከተዋለሁ፥ በቅርብ ግን አይደለም፤ ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፥ ከእስራኤልም በትረ መንግሥት ይነሣል፥ የሞዓብንም ግንባር ይመታል፥ የሤትንም ልጆች ያጠፋል።

18 ኤዶምያስም ርስቱ ይሆናል፥ ጠላቱ ሴይር ደግሞ ርስቱ ይሆናል፤ እስራኤልም በኃይል ያደርጋል።

19 ከያዕቆብም የሚወጣ ገዥ ይሆናል፥ ከከተማውም በሕይወት የተረፉትን ያጠፋል።”

20 በለዓምም አማሌቅን አይቶ ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፦ “የአሕዛብ መጀመሪያ የሆነ አማሌቅ ነበረ፤ ፍጻሜው ግን ወደ ጥፋት የሚያመራ ይሆናል።”

21 ቄናውያንንም አይቶ ምሳሌውን ይምስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፦ “ማደሪያህ የጸና ነው፥ ጎጆህም በዐለት ላይ ተሠርቶአል፤

22 ቄናዊው ግን ለጥፋት የተዘጋጀ ይሆናል። አሦር የሚማርክህ እስከ መቼ ድረስ ይሆን?”

23 ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፦ “እግዚአብሔር ይህን ባደረገ ጊዜ ወዮ! ማን በሕይወት ይኖራል?

24 ከኪቲም ዳርቻ መርከቦች ይመጣሉ፥ አሦርንም ያሠቃያሉ፥ ዔቦርንም ያስጨንቃሉ፤ እርሱም ደግሞ ወደ ጥፋት የሚያመራ ይሆናል።”

25 በለዓምም ተነሣ፥ ተመልሶም ወደ ስፍራው ሄደ፤ ባላቅም መንገዱን ተከትሎ ወደ ቤቱ ሄደ።