የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ

ማስታወቂያዎች

መላው መጽሐፍ ቅዱስ ብሉይ ኪዳን አዲስ ኪዳን


መጽሐፈ ዮዲት 2 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)
መጽሐፈ ዮዲት 2

በምዕራብ በኩል የተካሄደው ዘመቻ

1 በዓሥራ ስምንተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር በሃያ ሁለተኛው ቀን በአሦሩ ንጉሥ በናቡከደነፆር ቤት ከዚህ በፊት እንደ ተናገረው አገሮቹን ሁሉ ለመበቀል ምክክር ተደረደ።

2 ሹሞቹንና ታላላቅ ሰዎቹን ሁሉ ሰብስቦ ከእነርሱ ጋር ሚስጢራዊ እቅዱን በፊታቸው አስቀመጠ፥ የምድሪቱን ሁሉ ክፋት በአንደበቱ ተናገረ።

3 ከአፉ የወጣውን ቃል አልታዘዝም ያለ ሥጋ ሁሉ እንዲጠፋ ወሰኑ።

4 እንዲህም ሆነ እቅዱን ከጨረሰ በኋላ የአሦር ንጉሥ ናቡከደነፆር ሠራዊት ዋና የጦር አዛዥ በደረጃ ከራሱ ቀጥሎ ሁለተኛ የሆነውን ሆሎፎርኒስን ጠርቶ እንዲህ አለው፦

5 “የምድር ሁሉ ጌታ የሆነው ትልቁ ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ እነሆ ከፊቴ ሂድና በኀይላቸው የታወቁትን ሰዎች ከአንተ ጋር መቶ ሃያ ሺህ እግረኛ ወታደሮችና ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሰኞችን ውሰድ፤

6 ከአፌ የወጣውን ቃል አልታዘዙምና በምዕራብ ያለውን ምድር ሁሉ ተገናኛቸው፤

7 መሬትና ውሃ እንዲያዘጋጁ ንገራቸው፥ በቁጣዬ በእነሱ ላይ እወጣለሁና፤ የምድርም ገጽ ሁሉ በሠራዊቴ እግሮች ይሸፈናሉ፤ እንዲበረበሩም እተዋቸዋለሁ።

8 ቁስለኞቻቸው ሸለቆዎችን እና ወራጅ ውሃዎችን ይሞላሉ፤ ወንዝም በሬሳዎቻቸው ተሞልቶ ይፈሳል።

9 እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምርኮ አድርጌ እልካቸውዋለሁ።

10 አንተ ግን ቀድመህ ሂድና ግዛቶቻቸውን ሁሉ ያዝልኝ፤ ራሳቸውን አሳልፈው ከሰጡህ ፍርዳቸውን እስከሚቀበሉበት ቀን ድረስ ጠብቀህ አቆያቸው።

11 አንታዘዝህም ያሉትን ግን ዓይንህ አትተዋቸው፤ በያዝከው ምድር ሁሉ ለሞትና ለብዝበዛ አሳልፈህ ስጣቸው።

12 ሕያው ነኝና በመንግሥቴም ኃይል፥ የተናገርኩትን በእጄ እፈጽመዋለሁ።

13 አንተም ጌታህ ከተናገረህ ነገሮች አንድስ እንኳ እንዳትተላለፍ፥ ነገር ግን እንዳዘዝሁህ ፈጽማቸው፤ ሳትዘገይም ፈጽመው።”

14 ሆሎፎርኒስ ከጌታው ፊት ወጣ፥ የአሦርን ሠራዊት አዛዦችን፥ አለቆችና መኳንንት ሁሉ ጠራ።

15 ጌታው እንዳዘዘው የተመረጡ አንድ መቶ ሃያ ሺህ ሰልፈኞችና ዐሥራ ሁለት ሺህ ቀስት ወርዋሪ ፈረሰኞችን ቆጠረ።

16 ለጦርነትም አሰለፋቸው።

17 ዕቃዎቻቸውን የሚሸከሙ እጅግ ብዙ ግመሎችን፥ አህዮችንና በቅሎዎች፤ እንዲሁም ለምግብ የሚሆኑ ስፍር ቍጥር የሌላቸው በጎችን፥ በሬዎችንና ፍየሎችን ወሰደ፤

18 ለእያንዳንዱ ሰው የሚሆን ስንቅ፥ ብዙ ወርቅና ብር ከንጉሡ ቤት ወሰደ።

19 እርሱም ከሠራዊቱ ሁሉ ጋር ሆኖ ከንጉሡ ከናቡከደነፆር ቀድሞ ወደ ዘመቻ ለመሄድና በምዕራብ በኩል ያለ ምድርን ሁሉ በሠረገላዎች፥ በፈረሰኞችና በተመረጡ እግረኞች ሊሸፍኑ ወጡ።

20 ከእነሱም ጋር ብዛታቸው እንደ አንበጣና እንደ ምድር አሸዋ የሆኑ ብዙ ድብልቅ ሕዝብ ሄዱ፤ ብዛታቸውም ቍጥር አልነበረውም።

የሆሎፎርኒስ ጥቃት ደረጃዎች

21 ከነነዌ ከተማ ወጥተው ወደ ቤክቲሌት ሜዳ የሦስት ቀን ጉዞ ተጓዙ፤ ከቤክቲሌት አጠገብ በሚገኝ ከላይኛው ኬልቅያ በስተ ግራ በኩል ባለው ተራራ ሰፈሩ።

22 ከዚያም ሆሎፎርኒስ ሠራዊቱን ሁሉ፥ እግረኞችን፥ ፈረሰኞችንና ሠረገላዎቹን ይዞ ወደ ተራራማው አገር ሄደ።

23 ፉጥንና ሉድን ሰበራቸው፤ የሬስስን ልጆችን ሁሉና፥ በኬሌዎን በስተ ደቡብ አንጻር ባለ በረሃ የሚኖሩ የእስማኤልን ልጆች ማረካቸው።

24 ኤፍራጥስን ተከትሎ፥ በመስጴጦምያ አልፎ በአብሮን ወንዝ ትይዩ ያሉ ምሽግ ያላቸውን ከተሞች ደምስሶ እስከ ባሕሩ ድረስ ሄደ።

25 የኪልቅያን ግዛቶች ያዘ፤ የተቃወሙትንም ሁሉ መታ፤ በዓረብ ፊት ለፊት ወደሚገኘው ወደ ደቡብ ያፌት ግዛት መጣ።

26 የምድያምን ልጆች ሁሉ ከበባቸው፥ መኖሪያዎቻቸውን አቃጠለ፥ መንጎቻቸውንም ዘረፈ።

27 ስንዴ በሚታጨድበት ጊዜ ወደ ደማስቆ ሜዳ ወርዶ እርሻቸውን በሙሉ አቃጠለ፥ የበጐቻቸውንና የበሬዎቻቸውን መንጎች ለጥፋት ሰጣቸው፥ ከተሞቻቸውን በዘበዘ፥ ሜዳዎቻቸውን አጠፋ፥ ወጣቶቻቸውን ሁሉ በሰይፍ አፍ መታ።

28 በባሕሩ ዳርቻ፥ በሲዶናና በጢሮስ በሚኖሩ ሁሉ፥ በሱርና በኦኪን በሚኖሩ ሁሉና በያምኒያ በሚኖሩ ሁሉ ፍርሃትና መንቀጥቀጥ ወደቀባቸው፤ በአዛጦንና በአስቀሎና የሚኖሩ እጅግ ፈሩት።