ሐዋርያት ሥራ 2:4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ሁሉም መንፈስ ቅዱስን ተሞሉ፤ ይናገሩ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እንደ አደላቸው መጠንም እየራሳቸው በሀገሩ ሁሉ ቋንቋ ይናገሩ ጀመሩ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ መንፈስም እንዲናገሩ በሰጣቸው መጠን በሌሎች ቋንቋዎች ይናገሩ ጀመር። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፤ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ መንፈስ ቅዱስ እንዲናገሩ በሰጣቸው ችሎታ መጠን በሌሎች ቋንቋዎች መናገር ጀመሩ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር። |
“ከእነርሱ ጋር ያለው ቃል ኪዳኔ ይህ ነው” ይላል እግዚአብሔር፤ “በአንተ ላይ ያለው መንፈሴ በአፍህም ውስጥ ያደረግሁት ቃሌ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ ከአፍህ፥ ከዘርህም አፍ፥ ከዘር ዘርህም አፍ አይጠፋም፥” ይላል እግዚአብሔር።
ስለዚህ ቍጣዬን መላሁባቸው፤ ታገሥሁ፤ ፈጽሜም አላጠፋኋቸውም፤ በሜዳ በሕፃናት ላይ በጐልማሶችም ጉባኤ ላይ መዓቴን በአንድነት አፈስስባቸዋለሁ፤ ባል ከሚስቱ ጋር ሽማግሌውም ከጎበዙ ጋር ይያያዛልና።
ተነሥተህም ወደ ተማረኩ ወደ ወገንህ ልጆች ሂድ፤ እነርሱም ቢሰሙ ወይም ቢፈሩ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገራቸው” አለኝ።
እርሱ በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ ይሆናልና የወይን ጠጅና የሚያሰክርም መጠጥ ሁሉ አይጠጣም፤ ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮም መንፈስ ቅዱስ ይመላበታል።
ነገር ግን አብ በስሜ የሚልከው የእውነት መንፈስ ጰራቅሊጦስ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል፤ እኔ የነገርኋችሁንም ሁሉ ያሳስባችኋል።
ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኀይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሁሉ፥ በሰማርያና እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ምስክሮች ትሆኑኛላችሁ።”
ጴጥሮስም፥ “እንደ እኛ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ እንግዲህ በውኃ እንዳይጠመቁ ውኃን ሊከለክላቸው የሚችል ማነው?” አለ።
ጳውሎስም እጁን በጫነባቸው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ ወረደ፤ ያንጊዜም በሀገሩ ሁሉ ቋንቋ ተናገሩ፤ ትንቢትም ተናገሩ።
ከቀርጤስና ከዐረብም የመጣን፥ እነሆ፥ የእግዚአብሔርን ጌትነት በየሀገራችን ቋንቋ ሲናገሩ እንሰማቸዋለን።”
ሲጸልዩም በአንድነት ተሰብስበው የነበሩበት ቦታ ተናወጠ፤ በሁሉም ላይ መንፈስ ቅዱስ መላባቸውና የእግዚአብሔርን ቃል በግልጥ አስተማሩ።
ወንድሞቻችን ሆይ፥ ከእናንተ ወገን በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብ የሞላባቸውን ሰባት ሰዎችን ምረጡ፤ ለዚህ ሥራም እንሾማቸዋለን።
ይህም ነገር በእነርሱ ዘንድ የተወደደ ሆነ፤ ሃይማኖቱ የቀናና መንፈስ ቅዱስ ያደረበትን ሰው እስጢፋኖስን፥ ፊልጶስን፥ ጵሮኮሮስን፥ ኒቃሮናን፥ ጢሞናን፥ ጰርሜናን፥ ወደ ይሁዲነት የተመለሰውን የአንጾኪያውን ኒቆላዎስንም መረጡ።
እስጢፋኖስም የእግዚአብሔር ጸጋና ኀይል የመላበት ሰው ነበር፤ በሕዝቡም መካከል ታላላቅ ተአምራትንና ድንቅ ሥራን ይሠራ ነበር።
በእስጢፋኖስም ላይ መንፈስ ቅዱስ መላ፤ ወደ ሰማይም ተመለከተ፤ የእግዚአብሔርን ክብር፥ ኢየሱስም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየ።
ያንጊዜም ሐናንያ ሄደ፤ ወደ ቤትም ገባ፤ እጁንም ጫነበትና፥ “ወንድሜ ሳውል፥ በመንገድ ስትመጣ የታየህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታይና መንፈስ ቅዱስ ይመላብህ ዘንድ ወደ አንተ ልኮኛል” አለው።
የተስፋ አምላክ እግዚአብሔርም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል በተስፋ ያበዛችሁ ዘንድ በእምነት ደስታንና ሰላምን ሁሉ ይፈጽምላችሁ።
ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጐም ይሰጠዋል።
የሰውን ሁሉ ቋንቋ ባውቅ፥ የመላእክትንም ሁሉ ቋንቋ ባውቅ፥ ነገር ግን ፍቅር ከሌለኝ እንደሚጮህ ነሐስ፥ ወይም እንደሚመታ ከበሮ መሆኔ ነው።
ፍቅር ለዘወትር አይጥልም፤ ትንቢት የሚናገርም ያልፋል፤ ይሻራልም፤ በልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገርም ያልፋል፤ ይቀራል፤ የሚራቀቅም ያልፋል፤ ይጠፋል።
ሁላችሁም በቋንቋ ልትናገሩ እወዳለሁ፤ ይልቁንም ትንቢት ልትናገሩ እወዳለሁ፤ ሳይተረጕም በቋንቋ ከሚናገር ይልቅ ትንቢት የሚናገር እጅግ ይበልጣልና፤ ቢተረጕም ግን ማኅበሩን ያንጻል።
ለእነርሱም ከሰማይ በተላከ በመንፈስ ቅዱስ ወንጌልን የሰበኩላችሁ ሰዎች አሁን ባወሩላችሁ ነገር እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳላገለገሉ ተገለጠላቸው፤ ይህንም ነገር መላእክቱ ሊመለከቱ ይመኛሉ።
ወደዚያም ኮረብታ በደረሰ ጊዜ፥ እነሆ፥ የነቢያት ጉባኤ አገኙት፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ ወረደ፤ በመካከላቸውም ትንቢት ተናገረ።