የእግዚአብሔር ምሕረት ከሕይወትም በላይ ታላቅና ክቡር ነው። ጠዋት ጠዋት የእግዚአብሔርን ፍቅር ሳታይ ሕይወትህ ትርጉም ባጣ ነበር። ብዙ ስህተቶችህን እያየም እግዚአብሔር አይጥልህም፤ እጅግ ይወድሃል። የእግዚአብሔር ምሕረት በሕይወታችን ባይገለጥ ማን ሰላም ሊያገኝ ይችላል? ማንም አይችልም ብዬ አስባለሁ። እግዚአብሔር የሌለው ሰው ባዶ ነው፤ በኃጢአትና በጥፋት ዓለም ውስጥ ነው ያለው።
የእግዚአብሔርን ቸርነት ስታይ ግን ከማለዳ እስከ ማታ ላንተ የሚያደርገውን ሁሉ ትረዳለህ። መጥፎ ድርጊቶችህንና ክፋትህን ስታስብ፤ ልብህ በአድናቆ ይነካና የማያቋርጥ የምስጋና ፍሰት በውስጥህ ይፈልቃል። እስትንፋስ እያለህ መኖርህ ራሱ የእግዚአብሔር ምሕረት ምልክት ነው። ይቅር ብሎሃል፤ ክፋትህን አጥቦልሃል፤ የሚገባህን ቅጣት በራሱ ላይ ተሸክሞልሃል።
ስለዚህ አመስግን፤ አፍህን ክፈትና እግዚአብሔርን አመስግን። ላንተ ቸር ሆኖልሃል፤ አስቦልሃል፤ በፍቅር ዓይን ተመልክቶሃል፤ ታላቁንና የማያልቀውን ምሕረቱን አልከለከለህም። ዛሬም እስከ ዘላለም የኢየሱስን ታላቅ ፍቅር አስብበት፤ የከበረውን ደሙን አክብር፤ በፍቅሩ ውስጥ ተጠመቅ።
ለሙሴ፣ “የምምረውን እምረዋለሁ፤ የምራራለትንም ራራለታለሁ” ይላልና። እንግዲህ ይህ ከሰው ፍላጎት ወይም ጥረት ሳይሆን፣ ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው።
እግዚአብሔር ቸር ነውና አመስግኑ፤ ፍቅሩም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። ሕዝቦች ሁሉ ከበቡኝ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ስም አስወግዳቸዋለሁ። መክበቡንስ በየአቅጣጫው ከበቡኝ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ስም አስወግዳቸዋለሁ። እንደ ንብ መንጋ ከበቡኝ፤ ነገር ግን እንደሚነድድ እሾኽ ከሰሙ፤ በርግጥም በእግዚአብሔር ስም አስወግዳቸዋለሁ። ተገፍትሬ ልወድቅ ተንገደገድሁ፤ እግዚአብሔር ግን ረዳኝ። እግዚአብሔር ብርታቴና ዝማሬዬ ነው፤ አዳኝ ሆነልኝ። በጻድቃን ድንኳን የእልልታና የሆታ ድምፅ፣ እንዲህ እያለ ያስተጋባል፤ “የእግዚአብሔር ቀኝ እጅ ብርቱ ሥራ ሠራች፤ የእግዚአብሔር ቀኝ እጅ ከፍ ከፍ አለች፤ የእግዚአብሔር ቀኝ እጅ ብርቱ ሥራ ሠራች።” ተርፌ በሕይወት እኖራለሁ እንጂ አልሞትም፤ የእግዚአብሔርንም ሥራ ገና እናገራለሁ። መገሠጹን እግዚአብሔር እጅግ ገሥጾኛል፤ ነገር ግን ለሞት አሳልፎ አልሰጠኝም። የጽድቅን ደጆች ክፈቱልኝ፤ በዚያ ገብቼ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። የእስራኤል ሕዝብ፣ “ምሕረቱ ለዘላለም ነው” ይበል።
እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህንና ፍቅርህን ዐስብ፤ እነዚህ ከጥንት የነበሩ ናቸውና። የልጅነቴን ኀጢአት፣ መተላለፌንም አታስብብኝ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቸርነትህ ብዛት፣ እንደ ምሕረትህም መጠን አስበኝ።
እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም እንደ ባለ አእምሮ የምታቀርቡት አምልኳችሁ ነው።
ተራሮች ቢናወጡ፣ ኰረብቶች ከስፍራቸው ቢወገዱ እንኳ፣ ለአንቺ ያለኝ ጽኑ ፍቅር አይናወጥም፤ የገባሁትም የሰላም ቃል ኪዳን አይፈርስም” ይላል መሓሪሽ እግዚአብሔር።
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባትና አምላክ ይባረክ፤ እርሱ ከታላቅ ምሕረቱ የተነሣ በኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሣት ምክንያት ለሕያው ተስፋ በሚሆን አዲስ ልደት፣
ወንድሞች ሆይ፤ አንድ ሰው በኀጢአት ውስጥ ገብቶ ቢገኝ፣ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ በገርነት ልትመልሱት ይገባል። ነገር ግን አንተም እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ።
የርኅራኄ አባት፣ የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። እኛ ራሳችን ከእግዚአብሔር በተቀበልነው መጽናናት፣ በመከራ ያሉትን ማጽናናት እንድንችል፣ እርሱ በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል።
የእግዚአብሔር ምሕረት ግን፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚፈሩት ላይ ነው፤ ጽድቁም እስከ ልጅ ልጅ ድረስ በላያቸው ይሆናል፤ ኪዳኑን በሚጠብቁት ላይ፣ ትእዛዙንም ለመፈጸም በሚተጕት ላይ ይሆናል።
ስለዚህም ተነሥቶ ወደ አባቱ ሄደ። “ነገር ግን፣ እርሱ ገና ሩቅ ሳለ፣ አባቱ አይቶት ራራለት፤ ወደ እርሱም እየሮጠ ሄዶ ዐቅፎ ሳመው። “ልጁም፣ ‘አባቴ ሆይ፤ በሰማይና በአንተ ፊት በድያለሁ፤ ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም’ አለው።
በእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረት፣ በርሱም ዘንድ ማዳን አለና፣ እስራኤል ሆይ፤ በእግዚአብሔር ተስፋ አድርግ። እርሱም እስራኤልን፣ ከኀጢአቱ ሁሉ ያድነዋል።
እግዚአብሔር ግን ምሕረት ሊያደርግላችሁ ይታገሣል፤ ርኅራኄም ሊያሳያችሁ ይነሣል። እግዚአብሔር የፍትሕ አምላክ ነውና፣ እርሱን በመተማመን የሚጠባበቁት ብፁዓን ናቸው!
እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቸርነትህ መጠን፣ ምሕረት አድርግልኝ፤ እንደ ርኅራኄህም ብዛት፣ መተላለፌን ደምስስ። አምላኬ ሆይ፤ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ ቀና የሆነውንም መንፈስ በውስጤ አድስ። ከፊትህ አትጣለኝ፤ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድ። የማዳንህን ደስታ መልስልኝ፤ በእሽታ መንፈስም ደግፈህ ያዘኝ። እኔም ለሕግ ተላላፊዎች መንገድህን አስተምራለሁ፤ ኀጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ። የድነቴ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ደም ከማፍሰስ አድነኝ፤ አንደበቴም ስለ ጽድቅህ በእልልታ ይዘምራል። ጌታ ሆይ ከንፈሮቼን ክፈት፤ አፌም ምስጋናህን ያውጃል። መሥዋዕትን ብትወድድ ኖሮ ባቀረብሁልህ ነበር፤ የሚቃጠል መሥዋዕትም ደስ አያሰኝህም። እግዚአብሔር የሚቀበለው መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ አትንቅም። በበጎ ፈቃድህ ጽዮንን አበልጽጋት፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጥሮች ሥራ። የጽድቅ መሥዋዕት፣ የሚቃጠል መሥዋዕትና ሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕት ያን ጊዜ ደስ ያሰኙሃል፤ ኰርማዎች በመሠዊያህ ላይ የሚሠዉትም ያን ጊዜ ነው። በደሌን ፈጽሞ ዕጠብልኝ፤ ከኀጢአቴም አንጻኝ።
ነገር ግን የአዳኛችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ፍቅር በተገለጠ ጊዜ፣ ስላደረግነው የጽድቅ ሥራ ሳይሆን፣ ከምሕረቱ የተነሣ አዳነን። ያዳነንም ዳግም ልደት በሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ መታደስ ነው፤
ከፍ ከፍ ያለውና ልዕልና ያለው እርሱ፣ ስሙም ቅዱስ የሆነው፣ ለዘላለም የሚኖረው እንዲህ ይላል፤ “የተዋረዱትን መንፈሳቸውን ለማነሣሣት፣ የተሰበረ ልብ ያላቸውን ለማነቃቃት፣ ከፍ ባለውና በቅዱሱ ስፍራ እኖራለሁ፤ የተሰበረ ልብ ካለውና በመንፈሱ ከተዋረደው ጋራ እሆናለሁ።
ብፁዕ ነው፤ መተላለፉ ይቅር የተባለለት፣ ኀጢአቱም የተሸፈነለት፤ የክፉዎች ዋይታ ብዙ ነው፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን፣ ምሕረት ይከብበዋል። ጻድቃን ሆይ፤ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤትም አድርጉ፤ ቅን ልብ ያላችሁም ሁሉ እልል በሉ። ብፁዕ ነው፤ እግዚአብሔር ኀጢአቱን የማይቈጥርበት፣ በመንፈሱም ሽንገላ የሌለበት፤
በደሙም በሆነው እምነት፣ እግዚአብሔር የማስተሰረያ መሥዋዕት አድርጎ አቅርቦታል፤ ይህንም ያደረገው ቀድሞ የተፈጸመውን ኀጢአት ሳይቀጣ በትዕግሥት በማለፍ ጽድቁን ለማሳየት ነው፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀጢአትን ብትቈጣጠር፣ ጌታ ሆይ፤ ማን ሊቆም ይችላል? ነገር ግን በአንተ ዘንድ ይቅርታ አለ፤ ስለዚህም ልትፈራ ይገባሃል።
ቀድሞ የርሱ ወገን አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆናችኋል፤ ቀድሞ ምሕረትን አላገኛችሁም ነበር፤ አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል።
እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ቸር ነውና፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና። የግብጽን በኵር የመታ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና። እስራኤልን ከመካከላቸው ያወጣ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና፤ በኀያል እጅና በተዘረጋች ክንድ ይህን ያደረገ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና። ቀይ ባሕር ለሁለት የከፈለ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና። እስራኤልን በመካከሉ ያሳለፈ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና። ፈርዖንንና ሰራዊቱን በቀይ ባሕር ያሰጠመ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና። ሕዝቡን በምድረ በዳ የመራ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና። ታላላቅ ነገሥታትን የመታ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና። ኀያላን ነገሥታትን የገደለ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና። የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንን የገደለ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና። የአማልክትን አምላክ አመስግኑ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና። የባሳንን ንጉሥ ዐግን የገደለ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና። ምድራቸውን ርስት አድርጎ የሰጠ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና። ለባሪያው ለእስራኤል ርስት አድርጎ የሰጠ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና። በውርደታችን ጊዜ ያሰበን፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና። ከጠላቶቻችን እጅ ያዳነን፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና። ለፍጡር ሁሉ ምግብን የሚሰጥ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና። የሰማይን አምላክ አመስግኑ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና። የጌቶችን ጌታ አመስግኑ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና።
በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፣ “ጌታ ሆይ፤ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?” አለው። ኢየሱስም “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም” አለው።
ክፉ ሰው መንገዱን፣ በደለኛም ሐሳቡን ይተው። ወደ እግዚአብሔር ይመለስ፤ እርሱም ምሕረት ያደርግለታል፤ ወደ አምላካችን ይመለስ፤ ይቅርታው ብዙ ነውና።
ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስ በርሱ ለሚያምኑና የዘላለምን ሕይወት ለሚቀበሉ ወሰን የሌለው ትዕግሥቱን ከኀጢአተኞች ዋና በሆንሁት በእኔ እንደ ምሳሌ አድርጎ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ።
እንዲሁም አሕዛብ እግዚአብሔርን ስለ ምሕረቱ ያመሰግኑት ዘንድ ነው፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ “ስለዚህ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ለስምህም እዘምራለሁ።”
ከክፉ ኅሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን፣ ሰውነታችንንም በንጹሕ ውሃ ታጥበን፣ በእውነተኛ ልብና በሙሉ እምነት ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ።
“ቀረጥ ሰብሳቢው ግን በርቀት ቆሞ፣ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ማየት እንኳ አልፈለገም፤ ነገር ግን ደረቱን እየደቃ፣ ‘እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔን ኀጢአተኛውን ማረኝ’ ይል ነበር።
የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን እንድንጠራ አብ አትረፍርፎ ያፈሰሰልን ፍቅር ምንኛ ታላቅ ነው! እኛም እንዲሁ ልጆቹ ነን። ዓለም እኛን የማያውቀንም እርሱን ስላላወቀው ነው።
ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፣ እንዲሁ ለሚፈሩት ምሕረቱ ታላቅ ናት። ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ መተላለፋችንን በዚያው መጠን ከእኛ አስወገደ።
መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሯችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።
“የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እርሱ ቀብቶኛልና፤ ለምርኮኞች ነጻነትን፣ ለታወሩትም ማየትን እንዳውጅ፣ የተጨቈኑትን ነጻ እንዳወጣ፣
በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ፣ ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ እርሱ ራሱ መልሶ ያበረታችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል።
ስለዚህ በሁሉም ነገር ወንድሞቹን መምሰል ተገባው፤ ይህንም ያደረገው መሓሪና ታማኝ ሊቀ ካህናት ሆኖ፣ እግዚአብሔርን ለማገልገልና ለሕዝቡ የኀጢአትን ስርየት ለማስገኘት ነው።
ነገር ግን በምሕረቱ ባለጠጋ የሆነ እግዚአብሔር ለእኛ ካለው ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ፣ በበደላችን ሙታን ሆነን ሳለ፣ በክርስቶስ ሕያዋን አደረገን፤ የዳናችሁት በጸጋ ነው።
ልባችሁን እንጂ፣ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤ እርሱ መሓሪና ርኅሩኅ፣ ቍጣው የዘገየና ፍቅሩ የበዛ፣ ክፉ ነገር ከማምጣትም የሚታገሥ ነውና።